ሁለቱ ሀገራት በተለይም በጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ከመቼውም ጊዜ በላይ መተባበራቸው ተገልጿል
ሩሲያ እና ኢራን ከመቼውም ጊዜ መቀራረባቸውን አሜሪካ ገለጸች።
የአሜሪካ ስለላ ተቋም እንዳስታወቀው ሩሲያ እና ኢራን ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሁን ላይ መቀራረባቸውን አስታውቋል።
የጀርመን ድምጽ እንደዘገበው ከሆነ ሩሲያ እና ኢራን የቴህራንን ጎረቤት ሀገራት እና ዩክሬንን ሊጎዳ የሚችል ወታደራዊ ትብብሮችን እያደረጉ ነው ስትል አሜሪካ አስጠንቅቃለች።
ሁለቱ ሀገራት በተለይም በሰው አልባ የጦር አውሮፕላን እና ጄት ዘርፍ የበለጠ ተቀራርበው እየሰሩ እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
የአሜሪካ ነጩ ቤተ መንግስት የጸጥታ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ እንዳሉት ሩሲያ እና ኢራን ወታደራዊ ግንኙነታቸው እና ትብብሮቻቸው ከዚህ በፊት ያልነበረ እና ሙሉ መተባበርን እያደረጉ ናቸው ብለዋል።
የኢራን ፓይለቶች የሩሲያውን ሱ-35 የውጊያ አውሮፕላንን እንዲያበሩ ስልጠና እየወሰዱ ሲሆን ይህንን የሩሲያ የጦር አውሮፕላን ቴህራን ከአንድ ዓመት በኋላ እንደምትረከብ ይጠበቃልም ተብሏል።
ይህ መሆኑ ደግሞ የኢራን አየር ሀይል የበለጠ የሚያጠነክረው ሲሆን የቴህራን ጎረቤት ሀገራት አደጋ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ ሲሉ ቃል አቀባዩ አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቴህራን እና ሞስኮ የጋራ የድሮን ማምረቻ ማዕከል ለመክፈት ማቀዳቸውንም አሜሪካ አስታውቃለች።
አሜሪካ ከዚህ በፊት እንዳለችው ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደች ላለው ወታደራዊ ዘመቻ ኢራን ሰራሽ ድሮኖችን ተጠቅማለች ስትል መክሰሷ ይታወሳል።
ኢራን በበኩሏ ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ትብብሮችን እንደምታደርግ ገልጻ ድሮኖቹን ግን የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ለሩሲያ የተላለፉ እንደሆኑ ገልጻለች።
ዩክሬንም በኢራን ሰራሽ ድሮኖች እየተደበደበች መሆኗን ገልጻ ከቴህራን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ልታቋርጥ እንደምትችል አስጠንቅቃለች።