ፑቲን በጉባዔው ላይ ባይገኙም የአየር ንብረት ሩሲያ ቅድሚያ የምትሰጠው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሆኑንም ሞስኮ አስታውቃለች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በስኮትላንድ በሚካሄደው የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ እንደማይገኙ የክሬምሊን ቤተ መንግስት አስታወቀ።
በቀጣዩ ወር በሚካሄደው በግላስኮው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ ፑቲን ወደ ስፍራው ላይጓዙ እንደሚችሉ ተገልጿል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፒስኮቭ ፕሬዝዳንቱ በስብሰባው ላይ በአካል ሊገኙ ላይገኙ እንደሚችሉ መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
ምንም እንኳን ቭላድሚር ፑቲን በግላስኮው ስብሰባ በአካል ባይገኙም ሩሲያ ጉዳዩን ቅድሚያ እንደምትሰጠው ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ሩሲያ ቅድሚያ የምትሰጠው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሆኑንም ነው ዲሚትሪ ፒስኮቭ ያረጋገጡት።
ሲኤንቢሲ ኒውስ በበኩሉ ቭላድሚር ፑቲን ወደ ስኮትላንድ የማይጓዙት በኮሮና ቫይረስ ፍራቻ መሆኑን ዘግቧል።
የአየር ንብረት ጉባዔው ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ጊዜው ወደዚህ ዓመት እንዲራዘም መወሰኑ የሚታወስ ነው።
ከአንድ ሳምንት በፊት ከሲኤንቢሲ ኒውስ ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት ቭላድሚር ፑቲን በአየር ንብረት ጉባዔው ላይ በአካል ለመገኘት እንዳልወሰኑ መግለጻቸው ይታወሳል።
በዚህ ወቅትም ፕሬዝዳንቱ “እኔ ስጓዝ ብቻዬን አልጓዝም፤ የፕሬስ አገልግሎት፤ አጃቢዎች፤ አሽከርካሪዎች፤ ፕሮቶኮሎች እና ሌሎችም በመኖራቸው ጥንቃቄው ለኔ ብቻ አይደለም ለሌሎቹም ነው” ሲሉም ተናግረው ነበር።