ሩሲያ እና ሳኡዲ ሁሉም የኦፔክ ፕላስ አባለት የነዳጅ ምርት እንዲቀንሱ አሳሰቡ
መሪዎቹ ይህን ጥሪ ያቀረቡት የማህበሩ ስብሰባ ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነው
ከ1979 ጀምሮ በአሜሪካ ማዕቀብ እየማቀቀች ያለችው ትልቋ የኦፔክ አባል ኢራን በነዳጅ ምርት ቅነሳ ውስጥ አልተካተተችም
ሩሲያ እና ሳኡዲ ሁሉም የኦፔክ ፕላስ አባለት የነዳጅ ምርት እንዲቀንሱ አሳሰቡ።
ሁለቱ የአለም ትልቅ ነዳጅ አምራች ሀገራት የሆኑት ሩሲያ እና ሳኡዲ አረቢያ በትናንትናው እለት የነዳጅ አምራች ማህበር (ኦፔክ ፕላስ) አባላት ለአለም የኢኮኖሚ ደህነት ሲባል ምርት ለመቀነስ የተደረገውን ስምምነት እንዲቀላቀሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
መሪዎቹ ይህን ጥሪ ያቀረቡት የማህበሩ ስብሰባ ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነው።
የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በችኮላ በተዘጋጀ ጉዞ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማንን ለማግኘት ወደ ሪያድ ከሄዱ ከሰአታት በኋላ ክሬሚሊን የሩሲያ እና ሳኡዳ አረቢያን የጋራ መግለጫ ይፋ አድርጓል።
ባለፈው ሳምንት ኦፔክ፣ ሩሲያ እና ሌሎች አጋሮች እለታዊ የነዳጅ ምርትን በ2.2 ሚሊየን በርሜል ለመቀነስ ስምምነት ላይ ደረሰዋል። እንዲቀነስ ስምምነት ላይ ከተደረሰው 2.2 በርሜል ውስጥ 1.3 በርሜል የሚሆነው የሩሲያ እና ሳኡዲ አረቢያ ነው።
ክሬሚሊን በመግለጫው በኢነርጂ ዘርፍ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ትብብር እና የኦፔክ ፕላስ ጥረት የአለምን የነዳጅ ገበያ ለማረጋጋት ወሳኝ ነው ብሏል።
መግለጫው አክሎም የአምራቾችን፣ የደንበኞችን ፍላጎት ከግምት የሚያስገባ እንዲሁም የአለምን ኢኮኖሚ እድገት የሚደግፍ ገበያ እንዲፈጠር፣ የሁሉም ተሳታፊ ሀገራት የኦፔክ ፕላስ ስምምነትን መፈረም አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።
አልጋ ወራሹ እና ፑቲን በስብሰባቸው የኦፔክ ፕላስ ሀገራት በቡድኑ ስምምነት መገዛት እንዳለባቸው መነጋገራቸውን ሮይተርስ የሳኡዲ ዜና አገልግሎትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ከ1979 ጀምሮ በአሜሪካ ማዕቀብ እየማቀቀች ያለችው ትልቋ የኦፔክ አባል ኢራን በነዳጅ ምርት ቅነሳ ውስጥ አልተካተተችም።
ኢራን በሚቀጥለው አመት ሚያዚያ እለታዊ ምርቷን 3.6 በርሜል እንደምታደረስ ይገመታል።