በ2023 ብቻ 335 ሺህ ሩሲያውያን በዩክሬን ለመዋጋት ተመዝግበዋል - ሰርጌ ሾጉ
ይሁን እንጂ ሞስኮ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ዩክሬን የመላክ እቅድ እንደሌላት ነው የመከላከያ ሚኒስትሩ ያነሱት
ሩሲያ በዩክሬን ከ200 ሺህ በላይ ወታደሮች እንዳሏት ይነገራል
በ2023 ከ335 ሺህ በላይ ሩሲያውያን ወደ ዩክሬን ዘምቶ ለመዋጋት መመዝገባቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉ ገለጹ።
በመስከረም ወር ብቻ 50 ሺህ ሰዎች ጦሩን ተቀላቅለውና በበጎ ፈቃድ ለሀገራቸው ለመሰለፍ ተመዝግበዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
ሩሲያውያን ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር ያደነቁት ሰርጌ ሾጉ፥ በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ሃይል ወደ ዩክሬን የመላክ ፍላጎት የለንም ብለዋል።
“ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ሲሉ ለገለጹት ጦርነት በቂ ወታደርና የጦር መሳሪያ በዩክሬን እንደሚገኝም በማከል።
ሩሲያ በዩክሬን ከ200 ሺህ በላይ ወታደሮች እንዳሏት ይነገራል።
በቅርቡ በጡረታ የለቀቁት የአሜሪካ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጀነራል ማርክ ሚሊ ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ በዩክሬን ምድር ከሚገኙ 200 ሺህ ወታደሮች ጋር የሚደረግ ጦርነት ደም አፋሳሽ፣ ረጅም ጊዜ የሚወስድና ከባድ መሆኑ አይቀርም ብለዋል።
ጀነራሉ ዩክሬን ሰኔ ወር ላይ የጀመረችው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ የሚፈለገውን ፈጣን ውጤት ያላመጣውም ከሞስኮ ወታደሮች ብዛት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ያምናሉ።
የሃርቫርድ ኬነዲ ስኩል ያወጣው ጥናት በበኩሉ እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ሩሲያ የዩክሬንን 31 ስኩዌር ማይል መያዟን፤ በአንጻሩ ኬቭ ከሞስኮ ወታደሮች ያስለቀቀችው ከ16 ስኩዌር ማይል እንደማይበልጥ ያሳያል።
ጦርነቱ ሲጀመር ሩሲያም ሆነች ዩክሬን የያዙት አቋም 19ኛ ወሩ ላይ በሚገኘው ጦርነት የደበዘዘ ይመስላል።
ሩሲያ “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ስትከፍት ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ትጥቅ አስፈታለሁ፤ የምዕራባውያን የእጅ አዙር መፋለሚያ ሜዳ እንድትሆን አንፈቅድም ዛቻ አልተሳካም።
ዩክሬንም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሩሲያን ወታደሮች ጠራርጌ ከግዛቴ አስወጣለሁ ብትልም ምኞት ብቻ ሆኖባት ቀርቷል።
ያለማቋረጥ የቀጠለው የምዕራባውያን ሁለንተናዊ ድጋፍ ምናልባትም በቀጣይ የጦርነቱን መልክ ሊቀይረው እንደሚችል ይገመታል።