ዩክሬን ገድያቸዋለው ያለቻቸው የሩሲያ አድሚራል አልሞቱም - የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር
አዛዡ ቪክቶር ሶኮሎቭ ከሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ ሹማምንት ጋር በበይነ መረብ ሲመክሩ የሚያሳይ ቪዲዮ ተለቋል
ሩሲያ በመስከረም ወር ብቻ 17 ሺህ የዩክሬን ወታደሮችን መግደሏን አስታውቃለች
ዩክሬን በሚሳኤል ጥቃት ገድያቸዋለው ያለቻቸው የሩሲያ የጥቁር ባህር መርከቦች አዛዥ አድሚራል ቪክቶር ሶኮሎቭ በህይወት እንዳሉ የሚያሳይ ምስል የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ለቋል።
የቪዲዮ ምስሉ ሶኮሎቭ ከሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉ እና ሌሎች ጀነራሎች ጋር በበይነ መረብ ውይይት ሲሳተፉ ያሳያል።
የዩክሬን አየር ሃይል በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ ሶኮሎቭ እና ሌሎች 33 ከፍተኛ አመራሮች በሴቫስታፖል ወደብ ላይ በተፈጸሙ የሚሳኤል ጥቃቶች መገደላቸውን ማሳወቁ ይታወሳል።
ክሬምሊን ስለሶኮሎቭ ግድያ ምንም መረጃ ለመስጠት አለመፈለጉ ጥርጣሬውን አጉልቶት ነበር።
ይሁን እንጂ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር በዛሬው እለት አዛዡ በስራ ገበታቸው ላይ መሆናቸውን የሚያሳይ ምስል በሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን አሰራጭቷል።
ሚኒስቴሩ ባወጣው ቪዲዮ የመከላከያ ሚኒስሩ ሰርጌ ሾጉ በመስከረም ወር ብቻ ከ17 ሺህ በላይ የዩክሬን ወታደሮች መገደላቸውን ሲያነሱ ይደመጣሉ።
ስባት የአሜሪካ “ብራድሊ” ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ 2 ሺህ 700 የጦር መሳሪያዎችን ማውደም መቻሉንም አንስተዋል።
የዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ምንም ውጤት አላመጣም ያሉት ሚኒስትሩ፥ ኬቭ በአውደ ውጊያ ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰባት መሆኑንም ነው ያብራሩት።
“አሜሪካ እና አጋሮቿ ዩክሬንን ማስታጠቃቸውን ቀጥለዋል፤ የኬቭ መንግስትም ያልሰለጠኑ ወታደሮችን ያለርህራሄ ወደ ሞት እየጨመሯቸው ነው” ሲሉም ነው ሾጉ የተናገሩት።
ሩሲያ እስካሁን ከ17 ነጥብ 5 በመቶ በላይ የዩክሬን ሉአላዊ ግዛትን በቁጥጥሯ ስር ማስገባቷን መረጃዎ ያሳያሉ።
በሞስኮ የተያዙባትን ስፍራዎች ለማስለቀቅ በሰኔ ወር የጀመረችው ዘመቻ ግን የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልቻለም።
የሃርቫርድ ኬነዲ ስኩል መረጃ እንደሚያሳየው ሩሲያ ባለፈው ወር የዩክሬንን 35 ስኩዌር ማይል ቦታ በቁጥጥሯ ውስጥ አስገብታለች።
በአንጻሩ ኬቭ ከሞስኮ ያስለቀቀችው 16 ስኩዌር ማይል የሚሸፍን አካባቢን ነው ይላል መረጃው።