አሜሪካ ወደ አውሮፓ ሚሳይል የምትልክ ከሆነ ሩሲያ የአጸፋ ምላሽ ትሰጣለች- ክሬሚሊን
ሩሲያ ምዕራባውያን በቀጥታ በጦርነቱ የሚሳተፉ ከሆነ ወደ ሶስተኛ የዓለም ጦርነት ይቀሰቀሳል ስትል ማስጠንቀቋ ይታወሳል
የሩሲያን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ወረራ የሚሉት ምዕራባውያን ሀገራት ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት አሻክረዋል
የአውሮፓ ሀገራት የአሜሪካን ሚሳይል ከተቀበሉ ራሳቸውን አደጋ ላይ ይጥላሉ ሲሉ የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ በዛሬው እለት ተናግረዋል።
የአሜሪካን ሀይፐርሶኒክ ሚሳይል ወደ አውሮፓ መላክ በተመለከተ በሩሲያው የመንግስት ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የተጠየቁት ፔስኮቭ "እነዚህን ሚሳይሎች የመከላከል ሙሉ አቅም አለን። ነገርግን እነዚህን ሚሳይሎች የሚያስቀምጡት (የአውሮፓ ሀገራት) ዋነኛ ተጠቂ ይሆናሉ" ብለዋል።
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አላማቸውን ሩሲያ ያደረጉ የአሜሪካ ሚሳይሎች በአውሮፓ ተቀምጠው እንደነበር እና በምላሹ የሩሲያ ሚሳይሎችም አውሮፓን ኢላማ ማድረጋቸውን የገለጹት ፔስኮቭ ግጭት የሚነሳ ከሆነ የአውሮፓ ሀገራት ዋነኛ ተጠቂ ይሆናሉ ብለዋል።
"አውሮፓ አሁን ላይ በአደገኛ መንገድ እየተጓዘች ነው። ይህ ለአውሮፓ ጥሩ ጊዜ አይደለም። ስለዚህ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ታሪክ ራሱን ይደግማል።"
ሩሲያ በፈረንጆቹ የካቲት 2022 በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተች በኋላ አሜሪካን ጨምሮ ከምዕራባውያን ሀገራት ያላት ግንኙነት በ60 ከመታት ውስጥ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
የሩሲያን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ወረራ የሚሉት ምዕራባውያን ሀገራት ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት አሻክረዋል፤ በሩሲያ ላይ በሽዎች የሚቆጠሩ ማዕቀቦችንም ጥለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ምዕራባውያን የእስያዎቹ ሀያላን ሀገራት ህንድ እና ቻይና፣ ሩሲያ እንዲያገሏት ጫና በማሳደር ላይ ናቸው። ቻይና እና ህንድ ግን ጫናውን ወደ ጎን በመተው ከሩሲያ ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረው ቀጥለዋል።
ምዕራባውያን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ነው። በቅርቡ የአሜሪካ የተወካዮች ምክርቤት የ60 ቢሊዮን ወታደራዊ ድጋፍ ማድጸቁ ይታወሳል።
ሩሲያ ምዕራባውያን ሀገራት እርዳታ ከማድረግ አልፈው በቀጥታ በጦርነቱ የሚሳተፉ ከሆነ ወደ ሶስተኛ የዓለም ጦርነት ይቀሰቀሳል ስትል ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
የኔቶ መስፋፋት ለደህንነቷ እንደሚያሰጋት የምትገልጸው ሩሲያ ስትራቴጂክ የኑክሌር መሳሪያ በአጋሯ እና ጎረቤቷ ቤላሩስ ማስቀመጧ ይታወሳል።
አሜሪካ ይህን የአሜሪካ እርምጃ በወቅቱ ተቃውማዋለች።