ሩሲያ በዩክሬን የውጊያ ግንባሮች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች እያደረስኩ ነው አለች
ሞስኮ የኪቭ ጦር በሰላማዊ ሰዎች ላይ "አስከፊ" የሚሉ በደሎች እየፈጸመ ነው ስትል ከሳለች
ፕሬዝደንት ዜለንስኪ በመልሶ ማጥቃት 6 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ከሩሲያ ኃይሎች ነጻ ወጥቷል ብለዋል
ሩሲያ በዩክሬን የውጊያ ግንባሮች ላይ "መጠነ ሰፊ ጥቃቶች" እያደረስኩ ነው አለች፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬን ጦር ላይ "የአየር፣ የሮኬት እና መድፍ የተቀናጀ ከፍተኛ ጥቃት እያደረሱ ነው" ብሏል፡፡
የክሬምሊን ባለስልጣናት የኪቭ ጦር መልሶ በያዘው ግዛት ውስጥ በሲቪሎች ላይ በደል ፈጽሟል ሲሉ ከሰዋል።
የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ በካርኪቭ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ "አስከፊ" የሚሉ በደሎች መፈጸማቸው የሚያመላክቱ ዘገባዎች እየወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
“ብዙ የቅጣት እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው...ሰዎች እየተሰቃዩ ፣ እየተንገላቱ ነው "ሲሉም ነው ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች የተናገሩት።
ባለፈው ሳምንት የዩክሬን ኃይሎች የወሰዱት እርምጃን ተከትሎ የሩሲያ ጦር በዩክሬን ካርኪቭ ግዛት ውስጥ ከሚገኙት ሁለት አካባቢዎች (ባላክሊያ እና ኢዚየም ) ለማፈግፈግ መገደዳቸው ሮይተርስ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም የዩክሬን ባለስልጣነት ወታደሮቻቸው ለሩሲያ ኃይሎች ወሳኝ አቅርቦት ማዕከል የሆነችውን ኩፒያንስክ መቆጣጠራቸው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በሰጡት መገለጫ ወታደሮቻቸው በወሰዱት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ “6 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ከሩሲያ ነጻ መውጣቱ” ተናግረዋል።
የዩክሬን ባለስልጣነት ይህን ይበሉ እንጂ፤የተወሰደው የማፈግፈግ እርምጃ በምስራቅ ዩክሬን የመትገኘውን ዶንባስ ግዛት ነጻ ለማውጣት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ለማድረግ ያለመ መሆኑን የምትገለጸው ሩሲያ በዩክሬን ምድር ፈለገቸውን ዓለማ ከመፈጸም የሚያግዳት ኃይል እንደሌለ በመግለጽ ላይ ናት፡፡
ሩሲያ፤ “ዓላማዬን እስከማሳካ የሚቆም ወታደራዊ ዘመቻ የለም” ስትል በትናንትናው እለት መግለጿም አይዘነጋም፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻው መጀመሪያ ላይ የተቀመጡት አላማዎች እስኪሳኩ ድረስ ይቀጥላል" ብለዋል።
አሁን ላይ የሩሲያ አየር፣ ሮኬቶችና መድፍ ኃይሎች የኩፒያንስክ እና ኢዚዩም የከተማ ማዕከሎችን ጨምሮ በዩክሬን የጦር ኃይሎች ይዞታወች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በመሰንዘር ላይ እንደሆኑም ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ከኪቭ ጋር ሊኖሩ ስለሚችሉ የሰላም ንግግሮች ተጠይቀውም፤ በሞስኮ እና በኪቭ መካከል የሚደረጉ "የድርድር ተስፋዎች የሉም" የሚል ምላሽ መስጠታቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል።