ሩሲያ በተመድ የጸጥታው ም/ቤት ከአፍሪካ፣ ከደቡብ እስያና ከደቡብ አሜሪካ ምንም ሀገር አለመወከሉ ትክክል አይደለም ብላለች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ማሻሻያ እንዲደረግበት ሩሲያ በድጋሚ ጠየቀች፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ሞስኮ ዴይሊ ኮሜርሳንት ላይ ባሰፈሩት ጹሑፍ ምዕራባውያን በጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት እጅግ የበዛ ኃይል እንዳላቸው አሰታውቀዋል፡፡
ምክር ቤቱ አምስት ቋሚ አባላት ቢኖሩትም፤ ከአፍሪካ፣ ከደቡብ እስያ፣ ወይም ከደቡብ አሜሪካ አንድም ሀገር አለመወከሉ ትክክል እንዳልሆነ ሰርጌ ላቭሮቭ ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ ያልሆኑት 10 ሀገራት ያሉት ሲሆን ሶስት ሀገራት ከአፍሪካ፤ ሁለት ከእስያ ፓስፊክ፤ አንድ ከምስራቅ አውሮፓ፤ ሁለት ከደቡብ አሜሪካ እና ከካሪቢያን ቀሪ ሁለት ደግሞ ከምዕራብ አውሮፓ እንዲመረጡ ይደረጋል፡፡ ሰርጌ ላቭሮቭ፤የእነዚህ ቋሚ ያልሆኑት 10 አባል ሀገራት ምርጫም ቢሆን ምዕራባውያኑን ተጠቃሚ ያደረገ ነው ሲሉ መጻፋቸውን ሩሲያ ቱዴይ ዘግቧል፡፡
የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፤ በ2019 በፈረንጆቹ በቬትናም ሆሂ ሚን በተካሄደ አንድ ጉባዔ ላይም በማደግ ላይ ያለው ዓለም የጸጥታ ምክር ቤት ውክልና ሊኖረው ይገባል የሚል ሃሳብ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡ ምክር ቤቱ ከደቡብ እስያ፣ ከአፍሪካንና ከደቡብ አሜሪካ አንድም ተወካይ አለመኖሩ አካባቢዎቹ በተቋሙ ፍጹም አለመወከላቸውን እንደሚያመለክት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
አሁን ያለው የቋሚ አባል ሀገራት ውክልና ሀገራት ጥያቄ እንዳያነሱና ባልተጻፈው ሕግ የመምራት አባዜ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ ሚኒስትር ላቭሮቭ፤ በጆ ባይደን የሚመራው አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት እና የቡድን ሰባት አባል ሀገራትን ወደ ቀደመው የዓለም ስርዓት እየመለሳቸው መሆኑንም አነስተዋል፡፡
ላቭሮቭ፤ ሀገራቸው በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ አንድ የሚያደርግ አጀንዳ እያቀረበች መሆኑንና ሞስኮም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ከሚሰራ የትኛውም ሀገር ጋር በፍትሃዊነት ለመስራት ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡