ሚኒስቴሩ በኩርስክ በኩል በተደረገው ውጊያ ዩክሬን ከ12ሺ በላይ ወታደሮቿን እና በርካታ የጦር መሳሪያዎቿን አጥታለች ብሏል
ሩሲያ በኩርስክ ግዛት 10 መንደሮችን ነጻ ማውጣቷን አስታወቀች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የዩክኬን ኃይሎች ባለፈው ወር ድንበር ጥሰው ጥቃት በመፈጸም በኩርስክ ግዛት ውስጥ ይዘዋቸው የነበሩትን 10 መንደሮችን ነጻ ማውጣቱን አስታውቋል።
"በቅርቡ በተካሄዱ የመልሶ ማጥቃት እርምጃዎች በሰሜን የተሰማራው ጦር አባላት በሁለት ቀናት ውስጥ 10 መንደሮችን ነጻ አውጥተዋል"ብሏል ሚኒስቴሩ።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው አፓናሶቭካ፣ ብያኮቮ፣ ቪሽንቭካ፣ ቪክቶሮቭካ እና ሰደን ጎርዲቭ የተባሉትን ጨምሮ 10 የኩርስ መንደሮች በሩሲያ ኃይሎች እጅ ገብተዋል።
መግለጫው አክሎም የሩሲያ ኃይሎች ከዩክሬን በኩል የተቃጡትን ሁለት መልሶ ማጥቃቶችን እና በኦልጎቭካ በኩል ለማጥቃት የተደረገ ሙከራን ማክሸፋቸውን ገልጿል።
በኩርስክ በኩል በተደረገው ውጊያ ዩክሬን ከ12ሺ በላይ ወታደሮቿን እና በርካታ የጦር መሳሪያዎቿን አጥታለች ብሏል ሚኒስቴሩ።
ሚኒስቴሩ የማጥቃተ ዘመቻው ይቀጥላል ብሏል።
ዩክሬን በምዕራብ ሩሲያ ኩርስክ ግዛት ድንበር በመጣስ ድንገተኛ ጥቃት የፈጸመችው፣ በምስራቅ ዩክሬን ያለው የሩሲያ ኃይል ወደኋላ እንዲያፈገፍግ ለማድረግ አስባ ነበር። ነገርግን ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ጥቃቷን በማጠናከር በግንባር ለሚገኘው የዩክሬን ጦር ግብአት ለማድረስ ወሳኝ ማስተላለፊያ የሆነችውን የፖክሮቭስክ ከተማ ለመያዝ ተቃርባለች። በዚህ ምክንያት ዩክሬን በኩርስክ ግዛት ድንበር ጥሳ ጥቃት በመፈጸሟ ያሰበችውን ግብ ማሳካት አልቻለችም።
ዩክሬይን ምዕራባውያን የሰጧትን የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን ከግንባር ርቃ ሩሲያ ግዛት ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ እንዲፈቅዱላት እየጠየቀች ትገኛለች።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ይህን የዩክሬን ጥያቄ ሊቀበሉት እንደሚችሉ አመላክተዋል።
ሩሲያ ግን ባይደን ዩክሬን ሩሲያን በረጅም ርቀት ሚሳይል እንድትደበድብ የሚፈቅዱ ከሆነ ከአሜሪካ ጋር ቀጥተኛ ግጭት ይፈጠራል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።