የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው የሩሲያ አየር ኃይል 110 የዩክሬን ድሮኖችን መትቶ ጥሏል
ዩክሬን ቁልፍ የሆነውን የሩሲያ ፈንጆች ማምረቻ ፋብሪካ መምታቷን ገለጸች።
ዩክሬን ሩሲያ ግዛት ውስጥ ዘልቃ ሊፔስክ በተባለችው ግዛት ውስጥ በሚገኝ የአየር ኃይል ሰፈር ላይ በፈጸመችው ጥቃት የፈንጆች ማምረቻን እና የማከማቻ መሰረተልማት መምታቷን የኪቭ ጦር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው የሩሲያ አየር ኃይል 110 የዩክሬን ድሮኖችን መትቶ ጥሏል።ከእነዚህ ውስጥ በሞስኮ አንድ፣ በኩርስክ ግዛት 43 እና በደቡብ ምዕራብ ሊፔስክ ግዛት ደግሞ 27 መመታታቸውን ሚኒስቴር አክሎ ገልጿል።
በአይነቱ ግዙፍ ከሆኑት አንዱ የሆነው ይህ የፈንጅ ማምረቻ ፋብሪካ ሞስኮ በየካቲት 2022 ላይ በዩክሬን ላይ ለጀመረችው "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ጥቅም ላይ ውሏል። ፋብሪካው የአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ማዕቀብ ሰለባም ሆኗል።
የሩሲያው 'ሾት' የተባለው የቴሌግራም ቻናል ድሮኖቹ ንዝህኒ ኖቭጎሮድ ግዛት በድዜርሂኒስክ ከተማ የሚገኘውን ያ. ኤም ስቬርድሎቭ የተባለውን የመንግስት ተቋም ለመምታት ሙከራ ማድረጋቸውን ዘግቧል።
የኪቭ ጦር ባደረሰው ጥቃት የደረሰውን የጉዳት መጠን እያጣራ መሆኑን ገልጿል።
የጥቃቱ ኢላማ ምን እንደሆነ ያልገለጹት የድዜርሂኒስክ ግዛት አስተዳዳሪ በኢንዱስትሪ ዞኑ ላይ በደረሰው የድሮን ጥቃት አራት የእሳት አደጋ ሰራተኞች በፍንጥርጣሪ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በቴሌግራም ገጹ እንዳለው ስምንት የዩክሬን ድሮኖች በንዝህኒ ግዛት ተመተው ወድመዋል። ነዋሪዎች በቦታው ከፍተኛ ፍንዳታ መፈጠሩን እና ነጭ ጭስ ሲወጣ ማየታቸውን 'ሾት' ሪፖርት አድርጓል።
የሞስኮ ከንቲባ ሰሬጌ ሶብያኒን በቴሌግራም ገጻቸው ድሮን ራምነስኪይ በተባለ የከተማው ክፍል መውደቁን እና የደረሰ ጉዳት ግን አለመኖሩን ተናግረዋል።
ኪቭ ሞስኮ ለምትፈጽምባት ተከታታይ የአየር ጥቃት ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት በሚያግዙ መሰረተልማቶች ላይ ጥቃት በማድረስ ምላሽ እንደምትሰጥ ሁልጋዜ ትናገራለች።