ሩሲያ ከፍተኛ ባለስልጣንን እና የጦርነት ጸኃፊን ለመግደል የተወጠነውን ሴራ ማክሸፏን አስታወቀች
ኤፍኤስቢ ኢላማ የተደረገውን ባለስልጣን እና ጸኃፊ ማንነት ይፋ አላደረገም
ኤፍኤስቢ እንደገለጸው ከ 1 1/2 ኪሎግራም ከሚመዝን ቲኤንቲ ጋር የሚመጣጠነው ቦምቡ በተንቀሳቃሽ የሙዚቃ ድምጽ ማጉያ ውስጥ ተጠምዶ ነበር
የሩሲያ ፌደራል ሴኩሪቲ ሰርቪስ (ኤፍኤስቢ) ዩክሬን ከፍተኛ ባለስልጣንን እና የጦርነት ጸኃፊን በተንቀሳቃሽ የሙዚቃ ድምጽ ማጉያ ላይ ቦምብ በማጥመድ ለመግደል የወጠነችውን ሴራ ማክሸፉን በትናንትናው እለት አስታውቋል።
በሶቭየት ዘመን የነበረው የደህንነት ተቋም ኬጂቢ ምትክ የሆነው ኤፎኤስቢ የሩሲያ ዜግነት ያለው ግለሰብ ከዩክሬን ደህንነት ባለሙያ ጋር በቴሌግራም መተግበሪያ ግንኘነት ማድረጉን ገልጿል።
ይህ ሩሲያዊ ግለሰብ በዩክሬኑ የደህንነት ባሉሙያ ትዕዛዝ መሰረት ሞስኮ ውስጥ ቦምብ ከደበቀበት ማውጣቱን ኤፎኤስቢ ጠቅሷል።
ኤፍኤስቢ እንደገለጸው ከ 1 1/2 ኪሎግራም ከሚመዝን ቲኤንቲ ጋር የሚመጣጠነው ቦምቡ በተንቀሳቃሽ የሙዚቃ ድምጽ ማጉያ ውስጥ ተጠምዶ ነበር። ኤፍኤስቢ ኢላማ የተደረገውን ባለስልጣን እና ጸኃፊ ማንነት ይፋ አላደረገም።
ሩሲያ የከፈተችባትን ጦርነት ህልውናዋን አደጋ ውስጥ እንዳስገባው የምትገልጸው ዩክሬን የጠላቶቿን ስነልቦና ለመጉዳት አላማቸውን የጠበቁ ግድያዎችን እንደምታደርግ ግልጽ አድርጋለች።
ድርጊቱን የሽብር ተግባር አድርጋ የገለጸችው ሩሲያ በ 2022 የተገደለችውን የታዋቂ ሩሲያዊ ልጅ ደርያ ዱጊና የመሳሰሉ ንጹሃንን በመግደል ዩክሬንን ከሳለች።
ከሁለት ሳምንት በፊት የዩክሬን ደህንነት የሩሲያ የኑክሌር መከላከያ ኃይል ኃላፊ የሆኑትን ሌትናንት ጀነራል ክሪሎቭን ሞስኮ ከሚገኘው መኖሪያቸው በሚወጡበት ወቅት ሞተር ሳይክል ላይ ቦምብ በማጥመድ ገድሏል።
ኪቭ ጀነራሉን የተከለከሉ የኬሚካል የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማስተዋወቅ ከሳቸው ነበር። ሩሲያ ግን ክሱን ውድቅ አድርጋለች።
የዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን መልክተኛ ጡረታ የውጡት ጀነራል ኬይዝ ኬሎግ እንዲህ አይነት ግድያዎች ጥሩ አለመሆናቸውን ለፎክስ ኒውስ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሶስት አመታት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀሩት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሲቀጥል፣ ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ፈጣን ግስጋሴ እያደረገች ትገኛለች።