ክሬሚሊን ዩክሬን በሩሲያ ቁጥጥር ስር ባለው የኑክሌር ኃይል ጣቢያ ላይ ያደረሰችው ጥቃት "በጣም አደገኛ ነው" ሲል ገልጿል
ሩሲያ ቤተመንግስት ክሬሚሊን ዩክሬን በሩሲያ ቁጥጥር ስር ባለው የዛፖርዥያ ግዛት በሚገኘው የኑክሌር ኃይል ጣቢያ ላይ ያደረሰችው ጥቃት "በጣም አደገኛ ነው" ሲል ገልጿል።
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቮ "ይህ አደገኛ ትንኮሳ ነው" ብለዋል።
"ይህ በረጅም ጋዜ እጅግ አደገኛ ጉዳት የሚያስከትል ነው። እንዳለመታደል ሆኖ የኪቭ መንግስት የሽብር ተግባሩን ቀጥሏል" ሲሉ ተናግረዋል ፔስኮቮ።
ሩሲያ ዩክሬን ባለፈው እሁድ እለት በሩሲያ ቁጥጥር ስር ያለውን የዛፖርዥያ ኑክሌር ጣቢያ ሶስት ጊዜ ማጥቃቷን ገልጻ ምዕራባውያን ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቃለች።
ነገርግን ዩክሬን በጥቃቱ እጄ የለበትም ብላለች።
በአውሮፓ ትልቁ የሆነው የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በቁጥጥር ስር የዋለው ሩሲያ በየካቲት 2022 በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ በከፈተች በጥቂት ወራት ውስጥ ነበር።
ስትጀምር "ልዩ ወታራዊ ዘመቻ" እያካሄደች መሆኑን ስትገልጽ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ምዕራባውያን እየተሳተፉ በመሆናቸው ግጭቱን ጦርነት ብላ እየጠራችው ነው።
አራት የዩክሬን ምስራቃዊ ግዛቶችን በከፊል የያዘችው ሩሲያ ሙሉ በሙሉ እስከምትቆጣጠራቸው ድረስ ማጥቃቷን እንደምትቀጥል መግለጿ ይታወሳል።
በቅረቡ ወሳኝ የተባለችውን አቭዲቪካን ጨምሮ በርካታ መንደሮችን የተቀጣጠረችው ሩሲያ ወደፊት ለመግፋት ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
ዩክሬን ወደኋላ ለማፈግፈግ የተገደደችው የምዕራባውያን ወታደራዊ ድጋፍ በፍጥነት ባለመድረሱ ነው፣ አሁንም የማይደረስ ከሆነ ተጨማሪ ቦታዎችን ልትለቅ እንደምትችል እየገለጸች ነው።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪም ሩሲያ እያደረሰችው ያለው ተከታታይ የረጅም ርቀት ሚሳይል ጥቃት ከቀጠለ ዩክሬን የአየር መከላከያ ሚሳይል ሊያልቅባት ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።