የአሜሪካ ጦር ሩሲያ የኔቶ አባል ሀገራት ላይ ጥቃት ከሰነዘረች ወደ ዩክሬን ለመግባት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል
በሮማኒያ ያለውን የአሜሪካ ጦር በስጋት እንደምታየው ሩሲያ አስታወቀች።
የክሪምሊን ቤተመንግስት ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ሩሲያ በሮማኒያ ያለውን የአሜሪካ ጦር በስጋትነት እንደምታየው ተናግረዋል።
አሜሪካ 101ኛ ኤርቦርን ብርጌድ የተሰኘው ወታደራዊ እዟ ሩሲያ የኔቶ አባል ሀገራት ላይ ጥቃት ከሰነዘረች ወደ ዩክሬን ገብቶ ውጊያ እንደሚከፍት መናገሯን ከዘገባዎች ላይ መስማታቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚህም ምክንያት ሩሲያ በምሮማኒያ ያለው የአሜሪካ ጦር ለደህንነቷ እንደሚያሰጋት አስታውቃለች።
ሩሲያ ከዚህ በፊት ብሔራዊ ደህንነቷ ጥያቄ ውስጥ ከገባ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ስትል የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿን እንደምትጠቀም ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መናገራቸው ይታወሳል።
ሞስኮ ከሰሞኑ የኑክሌር ጦሯ ወታደራዊ ልምምድ እንዲያደርግ ያዘዘች ሲሆን ይህ ልምምድ ሮማኒያ ካለው የአሜሪካ ጦር ጋር ግንኙነት ስለመኖሩ የወጣ መረጃ የለም።
ይህ በዚህ እንዳለ በሞስኮ በእስር ላይ ያለችው አሜሪካዊቷ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብሪትኒ ግሪነር ጋር የእስረኞች ልውውጥ ሊኖር እንደሚችል ተገልጿል።
ተጫዋቿ ባሳለፍነው የካቲት ላይ በሞስኮ ኤርፖርት የሀሸሽ ዘይት በማዘዋወር ወንጀል ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር መዋሏ ይታወሳል።
የሞስኮ ከተማ ፍርድ ቤትም በብሪትኒ ላይ በቀረበለት የአደገኛ እጽ ዝውውር ክስ ዘጠኝ ዓመት እስር እና 15 ሺህ 500 ዶላር ቅጣት ጥሎባታል።