አሜሪካን ጨምሮ ስድስት ሀገራት “ኢትዮጵያ ማንነት ላይ ያተኮረ የሚመስል እስር እንድታቆም”አሳሰቡ
በኢትዮጵያ “ግለሰቦች ያለ ክስ እና ፍርድ ቤት ችሎት ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መልኩ”ታስረው እንደሚገኙም ሀገራቱ ገልጸዋል
ሀገራቱ “ድርጊቶቹ የዓለም አቀፍ ህግን የጣሱ ሊሆኑ ስለሚችሉ መቆም አለባቸው” ብለዋል
አሜሪካን ጨምሮ ስድስት ሀገራት የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ ኢትዮጵያውያንን በብሄራቸው ምክንያት እና ያለ ክስ ማሰሩን በተመለከተ የሚወጡ ዘገባዎች ያሳስቡናል ብለዋል፡፡
አውስትራልያ፣ካናዳ፣ዴንማርክ፣ኔዘርላንድስ፣ታላቋ ብሪታንያ እና አሜሪካ፣ በአሜሪካው ሰቴት ዲፓርትመንት በኩል ባወጡት መግለጫ አሁን በኢትዮጵያ አለ ያሉትን የእስር ሁኔታን በተመለከተ የጋራ መግለጫ አውጥቷል፡፡
ሀገራቱ የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ግለሰቦች በብሄራቸው ለመታሰር ምንም ምክንያት ሊሆን አይችልም ማለታቸውን መግለጫው ጠቅሷል፡፡
ሀገራቱ በመግለጫቸው በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጡት ሪፖርትም በማጠቃሻነት አንስተዋል፡፡
ተቋማቱ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆኑ ቄሶችን፣ አዛውንቶችን እና ልጆች ያሏቸው እናቶችን ጨምሮ በርካታ የትግራይ ተወላጆች እንደታሰሩ የሚያመላክቱ ሪፖርቶች ይዘው መውጣታቸውንም ነው የሀገራቱ የጋራ መግለጫ ጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን ተከትሎ መንግስት በቁጥጥር ስር ያደረጋቸው ሰዎች ሁኔታ ያሳስበኛል ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡
“በአዲስ አበባ ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ከጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሰዎች ከስራ ቦታቸው፣ ከመኖሪያ ቤታቸው እና ከመንገድ ላይ ጭምር በቁጥጥር ስር ውለው በተለያዩ የከተማዋ ፖሊስ ጣቢያዎች ተይዘው እንደሚገኙ”ማረጋገጡንም ኮመሽኑ አስታውቆ ነበር፡፡፡፡
በአዋጁ መንግስት የጠረጠረውን መያዝ ይችላል ያለው ኢሰመኮ “እስሩ ማንነትን/ብሔርን መሰረት ባደረገ መልኩ በሚመስል መከናወኑ” እንደሚያሳስበው መግለጹንም ጭምር አል-ዐይን ኒውስ በወቅቱ ዘግቧል፡፡
የስድስቱ ሀገራት የጋራ መግለጫ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ግለሰቦች ያለ ክስ እና ፍርድ ቤት ችሎት ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መልኩ ታስረው እንደሚገኙ ያትታል።
“ድርጊቶቹ የዓለም አቀፍ ህግን የጣሱ ሊሆኑ ስለሚችሉ መቆም አለባቸው”ም ነው ያሉት ሀገራቱ፡፡
“በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር እና የኢሰመጉ የጋራ የምርመራ ሪፖርት ላይ እንደተመለካተው ከግጭት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች እና የመብት ጥሰቶች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበን እንገልፃለንም” ብለዋል ሀገራቱ ባወጡት የጋራ መግለጫ፡፡
ሀገራቱ ሁሉም ወገኖች ለዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ህግ የማክብር ግዴታቸው ማክበር አለባቸውም ብሏል፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ላለው ግጭት ምንም አይነት ወታደራዊ መፍትሄ እንደሌለው ግልጽ ያለት ሀገራቱ ፤ ማንኛውንም እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙም ሆነ የሚፈጸሙ ማናቸውም ጥሰቶች እንደሚያወግዙ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ማንነትን መሰረት ያደረገ እርስ አለመኖሩን ይገልጻል፤ ማንነትን መሰረት ያደረግ እስር እየተካሄደ ነው የሚለውን ክስ አይቀበለውም፡፡
“ሁሉም የታጠቁ ተዋጊዎች ጦርነቱን ያቁሙ እንዲሁም የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ይውጣ” ሲሉም ተደምጧል ሀገራቱ በመግለጫቸው፡፡ ሀገራቱ ሁሉም ወገኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በዘላቂነት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመደራደር እድሉን እንዲጠቀሙም በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኢትዮጵያውያን በፖለቲካዊና ህጋዊ በሆኑ መንገዶች ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደትና ሀገራዊ መግባባት መፍጠር አለባቸው ሲሉም ምክራቸው ለግሷል ሀገራቱ በመግለጫቸው፡፡
እስካሁን ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ረገጣዎች ተጠያቂ የሆኑ ሁሉ አካላት በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባም አሳስበወል፡፡
በፌደራል መንግስት እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል አለመግባባት እየተባባሰ የመጣው የብልጽግና ፓርቲን መመስረት ተከትሎ ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ብሎ በማፈንገጡ ነበር፡፡
ህወሓት፡ የፌደራል መንግስት ህገወጥ ነው ያለውን ምርጫ ማካሄዱም የአልመግባባቱ ጡዘት ውጤት ነበር።
በዚህም በሁለቱ አካላት መካከል የነበረው አለመግባባት ጥቅምት 24፣2013 ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ወደ ወታራዊ ግጭት ያመራው እንዳመራ ይታወሳል፡፡
ክህደት ፈጽሟል ባለው ህወሓት ላይ “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በማወጅ የትግራይ ዋና ከተማና ብዙ ቦታዎችን መያዝ የቻለው መንግስት፤ ከ8 ወራት በኋላ ለትግራይ ህዝብ የጽሞና ግዜ ለመስጠት በሚል ከትግራይ ክልል ሰራዊቱን ማስወጣቱንም እንዲሁ የሚታወቅ ነው።
በክልሉ በነበረው ጦርነት ወቅት ዜጎች መፈናቃላቸውንና መገደላቸውን ኢሰመኮና ሌሎች አለምአቀፍ ተቋማት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
መንግስት ጦሩን ከክልሉ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ህወሓት ወደ አማራ አፋር ክልል በመግባት ጥቃት በመሰንዘር፤ ሰዎች እንዲገደሉና ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ማድረጉንም መንግስት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡