ምዕራባውያን መጨረሻው አስከፊ ወደሆነው የኑክሌር ጦርነት እየተንደረደሩ ነው - ሩሲያ
ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የኑክሌር ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል በደጋጋሚ ማስጠንቀቋ ይታወሳል
ላቭሮብ ምዕራባውያን ለዩክሬን የሚያደርጉት ድጋፍ አሜሪካ እና አጋሮቿን ከሩሲያ ጋር በቀጥታ እንዲጋጩ ጫፍ ላይ አድርሷቸዋል በለዋል
ምዕራባውያን መጨረሻው አስከፊ ወደሆነው የኑክሌር ጦርነት እየተንደረደሩ ነው ስትል ሩሲያ አስጠነቀቀች።
ሩሲያ፤ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) እና ፈረንሳይ ለዩክሬን የሚያደርጉት ወታራዊ ድጋፍ ኑክሌር የታጠቁ የዓለም ኃያላን ወደ ግጭት እንዲገቡ እየገፉ ነው ብላለች።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በፈረንጆቹ 2022 በዩክሬን ላይ ያወጁት "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ከ1962ቱ የኩባ ኑክሌር ቀውስ ወዲህ በሩሲያ እና ምዕራባውያን መካከል ያለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀዛቀዝ ማድረጉን የሩሲያ እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ይናገራሉ።
የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዩክሬን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ተጨማሪ ወታራዊ እርዳታ ካጸደቀ ከሁለት ቀናት በኋላ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ አሜሪካ እና ኔቶ ሩሲያ ስትራተጂካዊ ሽንፈት እንዲደርስባት ቋምጠዋል ብለዋል።
ላቭሮብ እንዳሉት ምዕራባውያን ለዩክሬን የሚያደርጉት ድጋፍ አሜሪካ እና አጋሮቿን ከሩሲያ ጋር በቀጥታ እንዲጋጩ ጫፍ ላይ አድርሷቸዋል።
"ምዕራባውያን በአደገኛ ሁኔታ ኑክሌር በታጠቁ የዓለም በኃያላን መካካል ወደሚደረግ እና መጨረሻው አስከፊ ወደሆነ ጦርነት እየተንደረደሩ ነው" ሲሉ ተናግረዋል ላቭሮቭ።
ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የኑክሌር ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል በተደጋጋሚ ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
የአሜሪካ ባለስልጣናትም ይህን የሩሲያ ማስጠንቀቂያ በትኩረት እንደሚያዩት ሲገልጹ ቆይተዋል።
ዩክሬን እና ምዕራባውያን አምባገነኗ ሩሲያ ከኢምፔሪያሊዝም ጋር የሚመሳሰል መሬት የመቀማት ጦርነት እያካሄደች ነው፤ በዩክሬን ያለው ኃይሏም ሽንፈት መከናነብ አለብ ይላሉ።
ሩሲያ ይህን ጦርነት የጀመረችው የምዕራባውያን ወታደራዊ ጥምረት የሆነው ኔቶ ወደ ቀድሞ የሶቬት ሀገራት እየተስፋፋ መሆኑን እና ይህም ለደህንነቷ እንደሚያሰጋት ከገለጸች በኋላ ነበር።
ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን የሚገኙ አራተ ግዛቶችን በከፊል ወደ ግዛቷ የጠቀለለች ሲሆን ግዛቶቹን ሙሉ ለሙሉ ለመጠቅለል አሁንም እየተዋጋች ትገኛለች።