በክሪሚያ አራት ሰዎች የተገደሉት እና ሌሎች ከ150 በላይ የሚሆኑ የቆሰሉት አሜሪካ ሰራሽ በሆነ ሚሳይል ነው ብሏል የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በክሪሚያ ሴቫስቶፖል ከተማ ከደረሰው ከባድ ጥቃት ጋር በተያያዘ የአሜሪካን አምባሳደር ጠርቷል።
በክሪሚያ አራት ሰዎች የተገደሉት እና ሌሎች ከ150 በላይ የሚሆኑ የቆሰሉት አሜሪካ ሰራሽ በሆነ ሚሳይል መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ ተቃውሞውን ለመግለጽ አምባሳደሩን በዛሬው እለት ጠርቷል።
ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አሜሪካ በዩክሬን በኩል ሆና በጦርነቱ እየተሳተፈች ነው፤ "የበቀል እርምጃም ይኖራል" ብሏል። ሚኒስትቴሩ ስለሚወስደው እርምጃ አላብራራም።
ኪቭ፣ ሩሲያ ወረራ ከፈጸመችበት ከፈረንጆቹ የካቲት 2022 ወዲህ በዋናነት ከምዕራባዊውያን በምታገኘው የጦር መሳሪያ እርዳታ ላይ ጥገኛ ሆናለች። ዩክሬን የምታገኘው እርዳታ በምስራቅ እና ደቡብ ዩክሬን 1000 ኪሎሜትር በሚሸፍነው የጦር ግንባር ከትንሽ ለውጦች ውጭ የሩሲያ ኃይሎችን ገትራ እንድትይዛቸው አስችሏታል።
የተወሰኑ ምዕራባውያን ሀገራት ዘመናዊ መሳሪያ ለኪቭ ማስታጠቅ ክሬሚሊንን ሊተነኩስ ይችላል በሚል ድጋፍ ለማድረግ ሲያመነቱ ይስተዋላሉ።
ነገርግን ዩክሬን በደንብ የታጠቀውን የሩሲያን ኃይል ለማስቆም ስትሞክር ምዕራባውያን ሀገራት ቀስ እያሉ ተጨማሪ እርዳታ እያቀረቡላት ነው።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጎን ዩክሬን ራሷን ለመከላከል በአሜሪካ የተሰጧትን ሚሳይሎች ሩሲያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን ለመምታት እንድትጠቀም ፈቅዷል።
ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ አሜሪካ፣ ኪቭ ከአሜሪካ በልገሳ ያገኘቻቸውን የጦር መሳሪያዎች በሩሲያ መሬት ላይ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ አትፈቅድም ነበር።
የሩሲያ ባለስልጣናት እንደተናገሩት ተመቶ የወደቀው የዩክሬን ሚሳይል ስብርባሪ በክሪሚያዋ የወደብ ከተማ ሴቫስቶፖል ወድቆ የሁለት ህጻናትን ህይወት ጭምር ቀጥፏል።
ሩሲያ እንደገለጸችው ከሆነ ሚሳይሉ ኤቲኤሲኤምኤስ የተባለ አሜሪካ ሰራሽ የረጅም ርቀት ጋይድ ሚሳይል ነው ብላለች። በዚህ ምክንያት በሩሲያ የአሜሪካን አምሳደር ላይኔ ትራሲ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠርታለች።
ለእንዲህ አይነት ሚሳይል ጥቃት የኢላማ ጥናት የሚደረገው በአሜሪካ ወታደራዊ ባለሙያዎች ነው ያለው ሚኒስቴሩ ለጥቃቱ አሜሪካም እንደ ዩክሬን እኩል ኃላፊነት አለባት ብለዋል።