የሀውቲ ታጣቂዎች ጥቃት ፈጽመውባት የነበረችው ነዳጅ ጫኝ መርከብ ሰጠመች
በአደጋው መርከቧ ላይ የነበረ አንድ ሰራተኛ ህይወቱ ሳያልፍ እንደማይቀር ተገልጿል።
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ላይ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ እስካሁን ከ60 በላይ ጥቃቶችን አድርሰው በአጠቃላይ አራት የመርከብ ሰራተኞችን ገድለዋል
የሀውቲ ታጣቂዎች ጥቃት ፈጽመውባት የነበረችው ነዳጅ ጫኝ መርከብ ሰጠመች።
እቃ ጫኝ መርከቧ የሀውቲ ታጣቂዎች ጥቃት ካደረሱባት ከቀናት በኋላ ስትሰጥም፣ ታጣቂዎቹ በጀመሩት ዘመቻ የደረሰ ሁለተኛ የመስጠም አደጋ መሆኑን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በአደጋው መርከቧ ላይ የነበረ አንድ ሰራተኛ ህይወቱ ሳያልፍ እንደማይቀር ተገልጿል።
'ቱቶር' የተሰኘችው መርከብ በቀይ ባህር ላይ የደረሰባት የመስጠም አደጋ የሀውቲ ታጣቂዎች ከእስራኤል-ሀማስ ጦርነት ጋር በተያያዘ የጀመሩትን ዘመቻ ማጠናከራቸውን የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ይህ ጥቃት የተቃጣው አሜሪካ በቀይ ባህር ቀጣና ያለውን የመርከቦች እንቅሰቃሴ ደህንነት ለመጠበቅ ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወዲህ ከባድ የተባለ የባህር ላይ ዘመቻ ከከፈች ከወራት በኋላ ነው።
የላይቤሪያ ሰንደቅ አላማ ስታውለበልብ የነበረችው እና ንብረትነቷ የግሪክ የሆነችው መርከብ በቀይ ባህር መስጠሟን ያሳወቀው የእንግሊዝ ጦር ማሪታይም እና ትሬድ ኦፐሬሽን ሴንተር ነው።
"ወታደራዊ ባለስልጣናት ስብርባሪ እና የፈሰሰ ነዳጅ መታዩን ሪፖርት አድርገዋል" ብሏል ማእከሉ።
"መርከቧ ሰጥማለች ተብሎ ይታሰባል።"
የሀውቲ ታጣቂዎች የሚቆጣጠሩት ሚዲያ የውጭ ምንጮችን ጠቅሶ የመርከቧን መስጠም ዘግቧል። ሮይተርስ በጉዳዩ የአሜሪካን ጦር ቢጠይቅም መልስ አለማግኘቱን ጠቅሷል።
ቱቶር በቀይ ባህር ባለፈው ሳምንት ጥቃት የደረሰባት ቦንብ በታጠቁ የሀውዊ ድሮኖች ነው።
የኃይት ሀውስ የብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ክርቢ በመርከቧ ላይ በደረሰው ጥቃት ዜግነቱ የፊሊፒንስ የሆነ ሰራተኛ መገደሉን ባለፈው ሰኞ እለት መናገራቸው ይታወሳል።
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ላይ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ እስካሁን ከ60 በላይ ጥቃቶችን አድርሰው በአጠቃላይ አራት የመርከብ ሰራተኞችን ገድለዋል።
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ በመርከቦች ላይ ጥቃት እያደረሱ ያሉት ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው የፍልስጤሙ ሀማስ አጋርነት ለማሳየት መሆኑን ዘመቻውን በጀመሩበት ወቅት ባለፈዉ ህዳር ወር ገልጸዋል።