ደቡብ ሱዳን የማህበራዊ ትስስር ገጾች በጥቂቱ ለ30 ቀናት እንዲዘጉ ወሰነች
ደቡብ ሱዳናውያን በሱዳን ኤል ገዚራ ግዛት ሲገደሉ የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች መለቀቃቸው በጁባ ቁጣ ቀስቅሷል
ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች በፍጥነት በመሰራጨታቸው 16 ሱዳናውያን መገደላቸው ተገልጿል
ደቡብ ሱዳን የማህበራዊ ትስስር ገጾች በጥቂቱ ለ30 ቀናት እንዲዘጉ ወሰነች።
በሱዳን ኤል ገዚራ ግዛት ደቡብ ሱዳናውያን ሲገደሉ የሚያሳዩ ምስሎች ባለፈው ሳምንት በማህበራዊ ትስስር ገጾች መሰራጨታቸው በጁባ ቁጣ ቀስቅሷል።
ቪዲዮዎቹ ደቡብ ሱዳናውያንን ለበቀል ጥቃት አነሳስቶ በጁባና ሌሎች ከተሞች 16 ሱዳናውያን መገደላቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል።
በሱዳናውያን የሚተዳደሩ በርካታ ሱቆችም ተቃጥለዋል፤ ከፍተኛ ዝርፊያም ተፈጽሞባቸዋል።
በደቡብ ሱዳናውያኑ ግድያ የሱዳን ጦር እጅ አለበት ብለው ያመኑ ደቡብ ሱዳናውያን በሀገሪቱ በሚኖሩ ሱዳናውያን ላይ የበቀል እርምጃ እንዲወሰድ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲቀሰቅሱ ነበር ብሏል ፖሊስ።
የሱዳን ጦር በበኩሉ በኤል ገዚራ የተፈጸመውን ግድያ "የግለሰቦች ጥፋት" ነው በሚል በደቡብ ሱዳን በሚኖሩ ሱዳናውያን ላይ ዘመቻ መከፈቱን ተቃውሟል።
የደቡብ ሱዳን ብሄራዊ የኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተሩ ናፖሊዮን አዶክም በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚተላለፉ መልዕክቶች ከፍተኛ ሁከት መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም ሁከቱን ለማርገብ ቢያንስ ለ30 ቀናት ማህበራዊ ገጾች እንዲዘጉ ለኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎች ደብዳቤ ጽፈዋል።
"ኤምቲኤን ደቡብ ሱዳን" እና "ዜን" የተባሉት የቴሌኮም ኩባንያዎች ባወጡት መግለጫ ደንበኞቻቸው ከሶስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ እና ሌሎች የማህበራዊ ትስስር ገጾችን መጠቀም እንደማይችሉ አስታውቀዋል።
በጁባ የሚገኝ የሬውተርስ ዘጋቢ ፌስቡክና ቲክቶክ መጠቀም እንዳልቻለ ገልጿል።
ደቡብ ሱዳናውያን መንግስት ከሱዳን ጋር በመነጋገር ሁከቱን ለማስቆም መፍትሄን ከማበጀት ይልቅ ማህበራዊ ገጾችን መዝጋቱ ተገቢ እንዳልሆነ እየተናገሩ ነው።