![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/12/243-174726-img-20250212-161606-266_700x400.jpg)
ሩሲያ የለቀቀችው አሜሪካዊ እስረኛ በሙያው መምህር ሲሆን በእጽ ማዘዋወር ተከሶ 14 አመታት እስር ተፈርዶበት ነበር
የሩሲያ ቤተመንግስት ክሬሚሊን በዋሽንግተንና ሞስኮ መካከል የእስረኛ ልውውጥ መካሄዱን በዛሬው እለት አረጋግጧል።
በሞስኮ ታስሮ የነበረው አሜሪካዊ ማርክ ፎጌል አሜሪካ ውስጥ ታስሮ በነበረ ሩሲያዊ ተቀይሮ ተፈትቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ፎጌል ተፈቶ አሜሪካ ሲገባ እንደተቀበሉት ሮይተርስ ዘግቧል። የእስረኛ ልውውጡ የተካሄደው ሁለቱ ሀገራት መካከል ንግግር ማድረግ ከተጀመረ በኋላ ነው።
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ልውውጡ በዋሽንግተንና ሞስኮ መካከል "ጥልቅ ግንኙነት" መደረጉን ተከትሎ የመጣ ነው ብለዋል።
"ቀደም ሲል እንደገለጽነው በሚመለከታቸው ኤጀንሲዎች አማካኝት በዚህ ዙሪያ ያለው ንግግር በቅርቡ በመጠናከሩ ፎጌልና አንድ ሩሲያዊ ተለቀዋል።"
ፔስኮቭ የሚለቀቀውን ሩሲያዊ ግለሰብ ማንነት ግልጽ ባያደርጉም በቀጣይ ቀናት እንደሚመጣ ገልጸዋል።
ፔስኮቭ አክለውም "ግለሰቡ ሩሲያ ግዛት ውስጥ ከገባ በኋላ ማንነቱ ይፋ ይደረጋል" ብለዋል።
ልውውጡን ለማመቻቸት ሌላ ሶስተኛ ሀገር ተሳትፎ እንደሆነ የተጠየቁት ፔስኮቭ "በዚህ ወቅት ሌላ ሪፖርት የምናደርገው የለም" ሲሉ መልሰዋል።
ሩሲያ የለቀቀችው አሜሪካዊ እስረኛ በሙያው መምህር ሲሆን በእጽ ማዘዋወር ተከሶ 14 አመታት እስር ተፈርዶበት ነበር።