የሩሲያ ጦር በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ
በድሮን ጥቃቱ በንብረትም ሆነ በሰው ህይወት ላይ ስለደረሰ የጉዳት መጠን የተገለጸ ነገር የለም
ዩክሬን፤ ዘጠኝ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በኪቭ የአየር መቃወሚያ ተመተው መውደቃቸውን አስታውቃለች
የሩሲያ ኃይሎች ዛሬ ማለዳ ላይ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ የድሮን ጥቃት መሰንዘራቸውን የኪቭ ከተማ ወታደራዊ አስተዳደር፡፡
አስተዳደሩ በቴሌግራም ላይ "ጠላት በዋና ከተማው ላይ ጥቃት ሰንዝሯል" ብሏል።
በከተማዋ ጥቃት ሲያደርሱ ከነበሩት ዘጠኝ የሩሲያ ዩኤቪዎች (ሰው አልባ አውሮፕላኖች) በኪቭ የአየር መቃወሚያ ተመተው መውደቃቸው የገለጸው አስተዳደሩ ህዝቡ ራሱን ከጥቃት ለመጠበቅ የአየር ማንቂያዎችን እንዲከታተልም አሳስቧል።
ይሁን እንጅ በድሮን ጥቃቱ በንብረትም ሆነ በሰው ህይወት ላይ ስለደረሰ ጉዳት መጠን ወታደራዊ አስተዳደሩ ያለው ነገር የለም፡
የሩሲያ ኃይሎች ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ዋና ከተማዋን እየደበደቡ ያሉት ኢራን ሰራሽ በሆነው “ሻሂድስ” የተሰኘውን የጦር መሳሪያ በመጠቀም እንደሆነም አስተዳደሩ ገልጿል፡፡
የሩሲያ ኃይሎች ከአራት ቀናት በፊት በከተማዋ ላይ ተመሳሳይ የድሮን ጥቃት ሰንዝረው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ንጹሃን በተኙበትና ድሮኖች ከእይታ በሚሰወሩበት ሌሊት ላይ በተሰነዘረው ጥቃት በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም፤ በሁለት የአሰተዳደር ህንጻዎች ጉዳት እንደደረሰ የኪቭ ከተማ ከንቲባ ቪታል ክሊትሽኮ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
በወቅቱ የዩክሬን የአየር መቃወሚያ በወሰደው እርምጃ 13 ድሮኖችን መትቶ በመጣል ውጤታማ ስራ መስራቱም ተገልጾ ነበር፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በወቅቱ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክትም በአየር ሃይላቸው እርምጃ ኩራት እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡
ሞስኮ ከቴህራን ያገኘቻቸው ድሮኖችን በዩክሬን ጦርነት የመጠቀሟ ጉዳይም አሁንም አብይ አጀንዶ ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡