ፕሬዝዳንት ፑቲን የኑክሌር አረር የታጠቁ ሚኤሎች እንዲሰሩ አዘዙ
አሜሪካ እና ሩሲያ የመካከለኛ እና አጭር ርቀት የኑክሌር አረር ሚሳኤሎችን ላለማምረት ስምምነት ነበራቸው
አሜሪካ ይህንን ስምምነት በመጣስ በፊሊፒንስ እና ዴንማርክ ተመሳሳይ ሚሳኤሎችን አስፍራለች ተብሏል
ፕሬዝዳንት ፑቲን የኑክሌር አረር የታጠቁ ሚኤሎች እንዲሰሩ አዘዙ፡፡
ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ ዓለማችን ከባድ የጦር መሳሪያ ማምረት ፉክክክር ውስጥ ገብታ የነበረ ሲሆን ዋነኞቹ ተፎካካሪዎች ደግሞ አሜሪካ እና ሶቪየት ህብረት ነበሩ፡፡
የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን እና የሶቭየት ህብረት ፕሬዝዳንት ሚካኤል ጎርባቾቭ መካከለኛ እና የአጭር ርቀት የሚጓዙ ኑክሌር አረር የተገጠመላቸው ሚሳኤሎችን ላለማምረት ከ37 ዓመት በፊት ስምምነት ተፈራርመው ነበር፡፡
ይሁንና ዶናልድ ትራምፕ በፈረንጆቹ 2019 ላይ ሩሲያ ይህንን ስምምነት እያከበረች አይደለም፣ አሜሪካ በዚህ ስምምነት ታጥራ እያለ ቻይና በጎን እያመረተች እና አነው በሚል ስምምነቱን በይፋ ሰርዘዋል፡፡
አውሮፓ ራሱን መከላከል እንደማይችል ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናገሩ
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጉዳዩ ዙሪያ እንዳሉት ስምምነቱን አሜሪካ በመጣስ በፊሊፒንስ እና ዴንማርክ ሚሳኤሎችን አስፍራለች ይህ ደግሞ ለእኛ ስጋት ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ሩሲያ ከ500 እስከ 5 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጓዙ ኑክሌር አረር የተገጠመላቸው ሚሳኤሎች እንዲሰሩ መፍቀዳቸውን የተናገሩ ሲሆን ይህም የሆነው አሜሪካ የደህንነት ስጋት በመደቀኗ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና እነዚህ የሩሲያ ኑክሌር ሚሳኤሎች የትኛው ሀገር ላይ እንደሚቀመጡ እስካሁን አለመወሰኑን ፕሬዝዳንት ፑቲን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የዓለማችን ዋነኛ የኑክሌር አረር የታጠቁት አሜሪካ እና ሩሲያ ግንኙነታቸው በየጊዜው እየተሸረሸረ የመጣ ሲሆን የዩክሬን ጦርነት ደግሞ ግንኙነቱን ወደ ከፋ ደረጃ አድርሶታል፡፡
አሜሪካንን ጨምሮ የኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳኤል እየለገሱ ሲሆን የተወሰኑ ሀገራት ኪቭ ሩሲያን እንድትመታ እየፈቀዱ ናቸው፡፡
ሩሲያም አውሮፓን እና አሜሪካንን መምታት የሚችሉ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን ወደ ወዳጅ ሀገራት ልታሰፍር እንደምትችል አስጠንቅቃም ነበር፡፡