የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የዩክሬን መንግስት የሶቬት አይነት ጭቆና እያደረሰበኝ ነው ስትል ከሰሰች
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ያላትን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለማገድ የሚያስችል ህግ ማጽደቋ ይታወሳል
የሩሲያ ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ ዩክሬን ያወጣቸው አዋጅ በሚሊየን የሚቆጠሩ አማኞችን እና ገዳማትን ከአገልግሎት ውጭ የሚደርግ ነው ብሏል
የሩሲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዩክሬን አስተዳደር የሶቭየት ህብረት አይነት ጭቆና እያደረሰ ነው ስትል ከሰሰች፡፡
ቤተክርስቲያኗ ከቀናት በፊት ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ያላቸው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተቋማትን እንቅስቃሴ ለማገድ የሚስችል ህግ ማጽደቁን ተከትሎ ነው ተቃውሞዋን የገለጸችው፡፡
አዲሱ ህግ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የትኛውንም አብያተክርስቲያናት፣ ተቋማት ፣ የሀይማኖት ህብረቶች እና ገዳማት እንቅስቃሴን ለማገድ የሚያስችላት ነው፡፡
የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ ሀይማኖት ከፖለቲካዊ ውግንና የጸዳ አማኞች የፈጣሪን መንገድ እንዲከተሉ ብቻ የሚሰራ ህብረት ነው ብሏል፡፡
አዲሱ ህግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኦርቶዶክስ አማኞችን እና በሀገሪቷ የሚገኙ በርካታ ገዳማትን ከአገልግሎት ውጭ የሚደርግ ነው ያለው መግለጫው፤ በዚህም በቀዳሚነት የሚጎዱት የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና አማኞች ናቸው ብሏል፡፡
በተጨማሪም ይህ አዋጅ በርካታ የእምነቱ ተከታዮችን ንብረት የሚሳጣ እና የመጸለያ ስፍራዎችን የሚነጥቅ ነው ብላለች ቤተክርስቲያኗ፡፡
በሮማን ኢምፓየር ፣ በፈረንሳይ አብዮት እንዲሁም በሶቭየት ህብረት ጊዜ በቤተክርስቲያኗ እና በክርስቲያኖች ላይ ይደርስ ከነበረው ጭቆና ጋር የሚመሳል ነውም ስትል ነው ቅሬታዋን የገለጸችው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው መጨረሻ ጉዳዩ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር የሚገናኝ ፣ መንግስት በሀይማኖት ውስጥ ያሻውን እንዲያደርግ የሚፈቅድ ህግ በመሆኑ ለአለምአቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅት ቅሬታውን እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
ምንም እንኳን በ2022 የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሩሲያ ፓትሪያሪክ በመውጣት እራሷን እያስተዳደረች የምትገኝ ቢሆንም ኬቭ ቤተክርስቲያኗ እና ቀሳውስቶቿ ከሞስኮ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው በሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ ታሰማለች፡፡
የኬቭ አስተዳደር የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደች ያለውን እና 30 ወራት ያስቆጠረውን ጦርነት በማበረታት እና ሰላዮችን በማስጠጋት ይከሳታል።
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም በቤተክርስቲያኗ አገልጋች ላይ በደርዘን የሚቆጠር የወንጀል ምርመራ በማድረግ በሀገር ክህደት ክስ ተከሰዋል።