የሩስያ የጸጥታ ሀይሎች በእስር ቤት ታግተው ነበሩ ሰራተኞችን ማስለቀቃቸው ተነገረ
በትላንትናው እለት እራሳቸውን የአይኤስ አባል እንደሆኑ የገለጹ ታሳሪዎች የእስርቤቱን ሰራተኞች አግተው እንደነበር ይታወሳል
የጸጥታ ሀይሎቹ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ባደረጉት ጥረት ሁሉሙ አጋቾች ተገድለዋል
በሩሲያ የእስር ቤት ጠባቂዎችን አግተው የነበሩ ታራሚዎች መገደላቸው ተሰማ፡፡
የሩስያ ብሄራዊ ዘብ ታጋቾችን ለማስለቀቅ እና እስር ቤቱን ለመቆጣጠር ባከናወነው ስራ አራቱም አጋቾች በአልሞ ተኳሾች (ስናይፐርስ) መገደላቸው ነው የተነገረው፡፡
የአይኤስ አባል እንደሆኑ የገለጹ ታራሚዎች በትናንትናው እለት በሩሲያ ደቡባዊ ቮልጎግራድ ክልል በሚገኝ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት እስር ቤት ውስጥ ነበር 8 የእስር ቤት ጠባቂዎችን እና 4 ታሳሪዎችን ያገቱት፡፡
በእግታው ሂደት ሶስት የእስር ቤት ፖሊሶች በስለት ተወግተው ህይወታቸው ሲያልፍ ሌሎች ታሳሪዎች ደግሞ መጠኑ የተለያየ ጉዳት እንደደረሰባቸው አርቲ ዘግቧል፡፡
የሀገሪቱ የእስር ቤቶች አገልግሎት ተቋም በጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡ የእስር ቤት ፖሊስ ቤተሰቦች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል፡፡
የኡዝቤኪስታን እና ታጃኪስታን ዜግነት ያላቸው አጋቾች መካከል አንድኛው የሰው ህይወት በማጥፋት ሶስቱ ደግሞ በአደገኛ እጽ ዝውውር ተፈርዶባቸው በእስር ቤት የሚገኙ ናቸው፡፡
የሩስያ ብሄራዊ ዘብ ልዩ ሀይል አባላት በእስር ቤቱ ዙርያ በሚገኙ ህንጻዎች ዙርያ በመደበቅ አነጣጥረው በተኮሷቸው አራት ጥይቶች የሁለቱ አጋችች ህይወት ወዲያው ሲያልፍ ሁለቱ የህክምና ክትትል እየተደረጋላቸው ባሉበት እንደሞቱ ተነግሯል፡፡
አጋቾቹ የአይኤስ አባል መሆናቸውን ከማሳወቅ በዘለለ እገታውን ለምን እንደፈጸሙት እና ተጨማሪ ፍላጎት እንዳላቸው አላሳወቁም፡፡
በስፍራው በሚገኙ የእስር ቤት ሰራተኞች ተቀርጾ በወጣው አንድ ቪድዮ ላይ ከአጋቾቹ መካከል አንዱ በሙስሊም እስረኞች ላይ የሚፈጸመው በደል እንዳማረራቸው ሲናገር መደመጡን ሮይተርስ መዘገቡ ይታወሳል
መሰል የእስር ቤት እገታ እንግዳ ባልሆነባት ሩስያ ባሳለፍነው ሰኔ በደቡባዊ ሮስቶቭ ክልል በተመሳሳይ ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ስድስት እስረኞች የእስር ቤቱን ሰራተኞች አግተው በጸጥታ ሀይሎች መገደላቸው ይታወሳል፡፡