
ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከጀመሩ አንስቶ 49 ጊዜ የእስረኛ ልውውጥ አድርገዋል
ሩሲያ እኛ ዩክሬን ከ470 በላይ የጦርነት እስረኞችን ተለዋወጡ።
ዩክሬን በጦርነቱ ምክንያት በሩሲያ ታስረው የነበሩ 230 ዜጎቿ ተለቀው ወደ ዩክሬን መግባታቸውን ገልጻለች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ 248 እስረኞች መለቀቃቸውን ነው ያስታወቀው።
በቀጣይ ወር ሁለት አመት የሚደፍነው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በርካታ እስረኞች የተለቀቁበት ስምምነት እንዲደረስ አረብ ኤምሬትስ የማደራደሩን ሚና ተወጥታለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስኬታማውን የእስረኞች ልውውጥ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፥ “የእስረኞች ልውውጡ ኤምሬትስ ከሩሲያ እና ዩክሬን ጋር የመሰረተችው ጠንካራ ወዳጅነት ማሳያ ነው” ብሏል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከጀመሩ አንስቶ 49 ጊዜ የእስረኛ ልውውጥ ማድረጋቸውን የዩክሬን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገልጿል።
ሁለቱ ሀገራት ባለፉት ስድስት ወራት ግን የእስረኛ ልውውጥ አላደረጉም።
ሩሲያ የእስረኞች ልውውጡ በተደረገበት እለት በቤልጎርድ 12 የዩክሬን ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን መጣሏን ገልጻለች።
ኬቭ ባለፈው ሳምንት በድንበር ከተማዋ ቤልጎርድ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ከ25 በላይ ሩሲያውያን መገደላቸውን ተከትሎ ሞስኮ የአጻፋ እርምጃ መውሰዷን ቀጥላለች።
በመዲናዋ እና በዩክሬን ሁለተኛዋ ግዙፍ ከተማ ካርኪቭ ያነጣጠሩት ጥቃቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጠናከሩ ናቸው ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቤልጎሮዱ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሲጎበኙ የበቀል ዛቻ ካሰሙ በኋላ የሩሲያ የሚሳኤልና ድሮን ጥቃት መባባሱን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።