ሩሲያ ምዕራባውያን ሀብቷን እንዳይወርሱ አስጠነቀቀች
አሜሪካ እና እንግሊዝ በቤልጄም እና በሌሎች ሀገራት እንዳይንቀሳቀስ የተደረገው የሩሲያን ሀብት ለመውረስ እየሞከሩ ናቸው
የቡድን ሰባት ሀገራት የሩሲያ ሀብት ለመውረስ የሚወስኑ ከሆነ ሊወረሱ የሚችሉ የአሜሪካ እና የአውሮፖ ሀብቶች ዝርዝር እንዳለው ክሬሚሊን አስጠንቅቋል
ሩሲያ ሀብቷ የሚወረስባት ከሆነ የምትወርሰው የምዕራባውያን ሀብት ዝርዝር ማዘጋጀቷን ክሬሚሊን አስታውቋል።
የቡድን ሰባት ሀገራት 300 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለውን የሩሲያ ሀብት ለመውረስ የሚወስኑ ከሆነ ሊወረሱ የሚችሉ የአሜሪካ እና የአውሮፖ ሀብቶች ዝርዝር እንዳለው ክሬሚሊን በዛሬው እለት አስጠንቅቋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው የቡድን ሰባት አባል ሀገራት በካቲት ወር በሚገናኙበት ወቅት የሩሲያን ሀብት መውረስ በሚቻልበት ሁኔታ ይመክራሉ።
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ እንዲህ አይነቱ የምዕራባውያን እንቅስቃሴ "እንደሌብነት" የሚቆጠር እና አለምአቀፍ ህግን፣ የአለምን የፋይናንስ ስርአትን እና ኢኮኖሚን የሚጎዳ ነው ብለዋል።
"ሌሎች ሀገራት በአሜሪካ እና በአውሮፖ ላይ ያላቸውን የኢኮኖሚ ዋስትና ሰጭ እምነት የሚሸረሽር ነው። ስለሆነም ይህ ድርጊት ከባድ ችግር ያስከትላል"።
ሩሲያ ልትወርሳቸው የምትችላቸው የምዕራባውያን ሀብት ዝርዝር እንዳላቸው የተጠየቁት ፔስኮቭ "አዎ። አለን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ነገርግን ፔስኮቭ ሊወረሱ የሚችሉ ሀብቶችን በስም ለመጥቀስ አልፈለጉም።
ፑቲን በፈረንጆቹ 2022 በዩክሬን ላይ ልዩ ያሉት ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈቱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ ከሩሲያ ባንኮች ጋር ዝውውር በማቆም 300 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የሩሲያ ሀብት እንዳይንቀሳቀስ አደርገዋል።
አሜሪካ እና እንግሊዝ በቤልጄም እና በሌሎች ሀገራት እንዳይንቀሳቀስ የተደረገው የሩሲያን ሀብት ለመውረስ እየሞከሩ ናቸው።
የሉአላዊ ሀገርን ሀብት መውረስ ህገ የሚጥስ መሆኑን ሩሲያ በተደጋጋሚ ብትገልጽም፣ ምዕራባውያን ግን ተወርሶ ለዩክራን መሰጠት አለበት የሚል አቋም ይዘዋል።