የምርኮኛ ልውውጡ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የመጀመርያው ነው ተብሎለታል
ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የመጀመርያ ነው የተባለለት የምርኮኛ ልውውጥ አደረጉ።
የሩሲያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ታትያና ሞስካልኮቫ ከራሽያ ቱደይ /አር.ቲ የዜና ቻነል/ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ እንደገለጹት፤ በመጀመርያው ልውውጥ “ዘጠኝ የሩሲያ ወታደሮች አስመልሰናል” ብለዋል።
ኮሚሽነሯ በዘጠኝ የሩሲያ ወታደሮች ምትክ፤ በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የነበሩትን የዩክሬኗ ከተማ ሜሊቶፖል ከንቲባ እንደተለቀቁም ነው የተናገሩት።
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ግልጽ ጦርነት የተጀመረ ሲሆን፤ ከ3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ሀገራቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በሪፖርት ገልጿል።
ሩሲያ ጎረቤቷ ዩክሬን ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከፈረንጆች የካቲት 24 2022 ጀምሮ ወታደራዊ ዘመቻ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ መጀመሯ ይታወቃል።
የዩክሬን ሃይሎች ጠንካራ ተቃውሟቸውን የፈጠሩ ሲሆን ምዕራባውያን ሩሲያ ኃይሏን እንድታስወጣ ከፍተኛ ማዕቀብ ጥለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን የሚያወግዘዉን የዉሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት የከፈተችው፣የኔቶ ጦር ዩክሬንን ጨምሮ ወደ ቀድሞ የሶቬት ህብረት ሀገራት እተሰፋፋ ነው፤ይህም ለደህንነቷ አስጊ እንደሚሆን በመግለጽ ነበር።የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እደቀጠለ ቢሆንም ሀገራቱ ችግሩን ለመፍታት ውይይታቸውን ጀምረዋል።