ሩሲያ፤ አረብ ኤምሬትስ በሞስኮ-ኪቭ መካከል የምትጫወተውን የአሸማጋይነት ሚና እንድትቀጥልበት ፍላጎቷ መሆኑ ገለጸች
ኤምሬትስ ባዳረገችው ጥረት ሩሲያ እና ዩክሬን በቅርቡ የእስረኞች ልውውጥ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው
ፑቲን፤ ሩሲያ የዛፖሪዝሂያ ኒውክሌር ጣቢያ ደህንነት ለማረጋገጥ ስለምታደርገው ጥረት ለአረብ ኤምሬትስ አቻቻው አብራርተዋል
ሩሲያ፤ አረብ ኤምሬትስ በሞስኮ-ኪቭ መካከል የምትጫወተውን የአሸማጋይነት ሚና እንድትቀጥልበት ፍላጎቷ መሆኑ ገለጸች።
ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በሩሲያ የሚገኙት የአረብ ኤሚሬትስ ፕሬዝዳት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህንያን ከሩሲያው አቻቸው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተወያይተዋል።
መሪዎቹ በቅዱስ ፒተርበርግ በሚገኝ ቤተ መንግስት ያደረጉት ውይይት በሁለትዮሽና ግንኙነት እንዲሁም በቀጠናዊ እና በዓለምአቀፋዊ ሁነቶችን ዙሪያ ያተኮረ እንደነበርም የኤምሬትስ የዜና አገልግሎት (ዋም) ዘግቧል።
በዚህም መሪዎቹ በሁለቱም ሀገራት መካካል ባለው የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር ደስተኛ መሆናቸው ገልጸዋል፡፡
በተጫመሪም የሩሲያው ፕሬዝዳንት አሁን ላይ በዩክሬን ጦርነት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ስጋት ውስጥ ስለከተተውና በአውሮፓ ግዙፍ ስለሆነው የዛፖሪዝሂያ ኒውክሌር ጣቢያ ደህንነት ጉዳይና ሞስኮ የኒውክሌር ጣቢያውን ደህንነት ለማረጋገጥ ስለምታደርገው ጥረት ለኤምሬትሱ አቻቻው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲን አረብ ኤምሬትስ በሞስኮ-ኪቭ መካከል የምትጫወተውን የአሸማጋይነት ሚና እንድትቀጥልበት ፍላጎታቸው መሆኑም ተናግረዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባዳረገችው ጥረት ሩሲያ እና ዩክሬን በቅርቡ የእስረኞች ልውውጥ ማድረጋቸው ይታወቃል።
ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በበኩላቸው ከጉዳዩ (እስረኞች ልውውጥ) ጋር በተያያዘ በዩክሬን በኩል ያለውን አቋም ምን እንደሆነ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ገለጻ አድርገዋል።
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የተጀመረውን ንግግር ለመቀጣል በሚቻልበት ሁኔታ ያላቸው ሃሳብም በውይይቱ ለፑቲን አጋርተዋል ፕሬዝዳንት ቢን ዛይድ።
ሩሲያ፤ አረብ ኤምሬትስ በዩክሬን ጉዳይ ላይ ላንጸባረቀቸው ሚዛናው አቋም እንደምታመሰግን የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከወራት በፊት በሞስኮ ጉብኝት ላደረጉት የኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብደላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን መግለጻቸውም አይዘነጋም፡፡
ሁለቱም ሀገራት በተለያዩ መስኮች ዘርፈ ብዙ ትብብር እንደሚያደርጉ ይተወቃል፡፡
በተለይም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከዓረቡ ዓለም ያደገች ሀገር እንደመሆኗ ሞስኮ-አቡዳቢ ጋር የምታደርገው ትብብር የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በሀገራቱ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ መጠን ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል።