ሩሲያ 500 ዶላር በሚያወጣ ድሮን 10 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ታንኮችን ማውደሟ ተገለጸ
ዩክሬን በበኩሏ እርዳታ በዘገየ ቁጥር ሩሲያ የበለጠ ወደ ድል እየቀረበች ነው ስትል አስጠንቅቃለች
ከተመቱት የጦር ታንኮች መካከል ተፈላጊ እና ውድ የሚባሉ የአሜሪካ እና ጀርመን ታንኮች ይገኙበታል
ሩሲያ 500 ዶላር በሚያወጣ ድሮን 10 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ታንኮችን ማውደሟ ተገለጸ፡፡
ሶስተኛ ዓመቱን የያዘው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
ጦርነቱን ሩሲያ ካሸነፈች ለአውሮፓ የደህንነት ስጋት ይደቅናል በሚል የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ወይም ኔቶ አባል ሀገራት በተለያየ መንገድ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በተለይም ዩክሬን የምድር ላይ ውጊያዎችን የበላይነት እንድትይዝ በሚል ከምዕራባዊያን ሀገራት የተለገሱ ውድ የጦር ታንኮች ርካሽ ዋጋ ባላቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች መመታታቸው ተገልጿል፡፡
የጀርመኑ ሊዮፓርድ እና የአሜሪካ አብርሃም ታንኮች ውጊያ ቀያሪ እንደሆኑ ቢገለጽም ሩሲያ በቀላሉ በድሮን እየመታቻቸው እንደሆነ ኒዮርክ ታየምስ ዘግቧል፡፡
በዘገባው ላይ እንደተገለጸው አሁን ባለንበትን ዘመን የሚደረጉ የምድር ላይ ውጊያዎችን በበላይነት ለመቋጨት ይረዳሉ የሚባሉት እነዚህ ታንኮች ርካሽ በሆኑ ድሮኖች መመታታቸው ግርታን ፈጥሯል፡፡
ሩሲያ 500 ዶላር ዋጋ ባላቸው ድሮኖች 10 ሚሊዮን የሚያወጣ የጦር ታንክን ከጥቅም ውጪ ማድረጓ ሀገራቱ ስለ ቀጣይ ውጊዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ መነሻ እንደሚሆን ኒዮርክ ታየምስ ያነጋገራቸው የጦር ተንታኞች ተናግረዋል፡፡
ዘመናዊ ውጊያ ቀያሪ የሚባሉ ታንኮች መሬት ውስጥ በተቀበሩ ፈንጂዎች ሲመቱ የሚታወቅ ቢሆንም ለዚህ መፍትሔ ተዘጋጅቶላቸው የነበረ ቢሆንም በድሮን በቀላሉ መመታት መቻላቸው ለዩክሬን ድጋፍ እያደረጉ ያሉ ሀገራትን ግራ አጋብቷል ተብሏል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ ሩሲያ የአየር ለይ ጥቃቶችን በሰፊው እያደረሰችባት መሆኗን ገልጻ የአየር ለይ ጥቃት ማምከኛ የጦር መሳሪያዎችን እንዲለግሷት ጥሪ አቅርባለች፡፡
ከምዕራባዊያን የሚሰጠው የጦር መሳሪያ እርዳታ በዘገየ ቁጥር ሩሲያ የበለጠ ወደ ድል እየገሰገሰች እኛ ደግሞ እየተሸነፍን መሆኑን እወቁት ስትል ዩክሬን ተማጽናለች፡፡