አሜሪካ ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ በሩሲያ ባንኮች ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል
ሩሲያ የዶላር እና ዩሮ ግብይትን አገደች፡፡
ሶስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን አሜሪካ በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀቦችን ጥላለች፡፡
የሩሲያ ባንኮች ላይ ያነጣጠረው አዲሱ የአሜሪካ ማዕቀብ ሞስኮ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን የውጪ ንግድ ለመጉዳት ያለመ እደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የሩሲያ ምርት ገበያም በዶላር እና ዩሮ የሚደረጉ ግብይቶችን ላለማካሄድ መወሰኑን የገለጸ ሲሆን ከሁለቱ ውጪ በሌሎች መገበያያ ገንዘቦች ግን ማገበያየቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
ሩሲያ ከዩክሬን ጦርነት በኋላ የመገበያያ ገንዘቧን ከዶላር እና ዩሮ ጥገኝነት የማላቀቅ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች፡፡
ሩሲያ ካደረገቻቸው የንግድ ልውውጦች ውስጥ 53 በመቶውን በቻይና ዩዋን ያደረገች ሲሆን ቀሪው ደግሞ ዶላርን ጨምሮ ዩሮ እና የሌሎች ሀገራት መገበያያ ገንዘብ አድርጋለች፡፡
በአሁኑ ወቅት የሩሲያ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ሩብል ከዶላር አንጻር በቀን አንድ ቢሊዮን ሩብል በመገበያየት ላይ ስትሆን ከዩሮ አንጻር ደግሞ 300 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም በዩዋን ደግሞ 8 ቢሊዮን ሩብል በመገበያየት ላይ ትገኛለች፡፡
ሩሲያ ለምን የሚሳኤል ጠበብቶቿን በሀገር መክዳት ወንጀል ጠረጠረች?
አዲሱ የአሜሪካ ማዕቀብ የቻይናውን ዩዋን ተፈላጊነት ከፍ በማድረግ ለቤጂንግ ጥቅም የሚስገኝ ሲሆን የሩሲያው ሩብል ደግሞ የዋጋ መቀነስ ሊያጋጥመው እንደሚችል ተገምቷል፡፡
የሩሲያ ምርት ገበያ ባወጣው መግለጫ አሜሪካ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል ይጠበቅ ነበር ያለ ሲሆን ለዚህም ሲባል ከተለያዩ ሀገራት ጋር አስቀድሞ የንግድ ልውውጥ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የቡድን ሰባት ሀገራት መሪዎች ጉባኤ በጣልያን በመካሄድ ላይ ሲሆን በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የታገዱ የሩሲያ ንብረቶችን ማስያዣ በማድረግ ለዩክሬን 50 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ተስማምተዋል ተብሏል፡፡