ሩሲያ አሜሪካ እና አውሮፓ በረጅም ርቀት ሚሳኤሎች እንዲመቱ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ልታደርግ እንደምትችል ገለጸች
የሩሲያ አዲስ እቅድ ዩክሬን ሞስኮን እንድትመታ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረጉ ላሉ ምዕራባዊያን ሀገራት የአጸፋ እርምጃ ነው ተብሏል
ዩክሬን በመሀል ሩሲያ ጥቃት እንድትፈጽም ከተለያዩ ሀገራት ድጋፍ በማግኘት ላይ ነች
ሩሲያ አሜሪካ እና አውሮፓ በረጅም ርቀት ሚሳኤሎች እንዲመቱ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ልታደርግ እንደምትችል ገለጸች።
ለአንድ ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል ወደ ዩክሬን ግዛቶች መግባቱን ተከትሎ በአውሮፓ የተጀመረው ጦርነት ሶስተኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል።
ይህ ጦርነት መልኩን እየቀያየረ የቀጠለ ሲሆን ኣሜሪካንን ጨምሮ በርካታ የኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን የቀጥታ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው።
የሩሲያ ጦር ከዚህ በፊት በህዝበ ውሳኔ ወደ ሞስኮ ከተጠቃለሉ አራት ግዛቶች በተጨማሪ ሌሎች አካባቢዎችን እየተቆጣጠረ መምጣቱን ተከትሎ ዩክሬን በመሀል ሩሲያ ጥቃቶችን ለማድረስ አዲስ እቅድ ነድፋለች።
ለዚህ እቅዷም ምዕራባዊያን ሀገራት የረጅም ርቀጥ ሚሳኤሎችን ድጋፍ እንዲያደርጉላት እና ለጋሽ ሀገራት የጦር መሳሪያዎቹን ከጦር ግንባር ባለፈ መሀል ሩሲያን እንድትመታ እንዲፈቅዱላት ጠይቃለች።
እንደ ብሪታንያ ፣ፈረንሳይ ፣ዴንማርክ እና ሌሎች ሀገራት በለገሱት የረክም ርቀት የጦር መሳሪያዎች ዩክሬን በመሀል ሩሲያ ጥቃት እንድትፈጽም ይሁንታን ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት በለገሷቸው የጦር መሳሪያዎች ሩሲያ ከተጠቃች እኛም የአጸፋ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል
ከሚወሰዱ የአጸፋ እርምጃዎች መካከልም አሜሪካን እና የአውሮፓ ሀገራትን መምታት ለሚፈልጉ አጋሮቻችን የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን ልናስታጥቅ እንችላለን ሲሊም ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናግረዋል።
ሩሲያ ኔቶን ልታጠቃ ትችላለች? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ምዕራባዊያን ሀገራት እጃቸው ያለበት ጥቃት በተሰነዘረብን ቁጥር የበለጠ ወደ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት እንጠጋለን ብለዋል።
ምዕራባዊያን ሀገራት ሩሲያ ኔቶን ልታጠቃ ትችላለች እያሉ ይናገራሉ ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን ሞስኮ ኔቶን ቀድማ ላታጠቃ ትችላለች፣ ምዕራባዊያን ሀገራት የሩሲያን ኑክሌር አረር ህግን ሊያነቡ ይገባል ብለዋል።