የዩክሬን ባለስልጣናት ለምሽግ ግንባታ የተመደበ 500 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መዝብረዋል ተባለ
ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች ተሳትፈውበታል በተባለው ምዝበራ የወንጀል ምርመራ ተጀምሯል
የሀገሪቱ ፓርላማ መንግስት በጉዳዩ ዙርያ ተጨማሪ ማብራርያ እና ምላሽ እንዲሰጥ አዟል
ለምሽግ ግንባታ እንዲውል የተመደበ 491 ሚልየን ዶላር በዩክሬን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች መመዝበሩ ተነግሯል፡፡
ወደ ፊት እየገፋ የሚገኝውን የሩሲያ ጦር ለመከላከል ጠንካራ ውግያ በሚደረግበት ካራኮቭ ክልል ምሽጎችን ለመገንባት ነው ገንዘቡ የተመደበው፡፡
የዩክሬን ህግ አስከባሪ አካላት ከጉዳዩ ጋር በተገናኝ 30 መዝገቦችን በማጣራት ላይ እንደሚገኙ የሀገሪቱ ፓርላማ አባል ሚካኤል ቦንዳር ተናግረዋል፡፡
የዩክሬን ፓርላማ አጣሪ ኮሚቴ ጠፋ በተባለው ገንዘብ ምክንያት በቂ የመከላከያ ምሽጎች ባለመገንባታቸው የሩሲያ ጦር ወደ ፊት እንዲገሰግስ እድል ፈጥሯል ያለ ሲሆን ገንዘቡ በሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮች ስለመመዝበሩ ፍንጮች ማገኝቱን አስታውቋል፡፡
ኮሚቴው የሀገሪቱ የመከላከያ ሚንስቴር ለወታደራዊ ግንባታ የተመደበ በጀት አጠቃቀምን የተመለከተ አስቸኳይ ሪፖርት እንዲያቀርብለትም ጠይቋል፡፡
በባለፈው ወር የዩክሬን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች በሚሊየን ዶላር የሚገመት የምሽግ ግንባታ ግብአት አቅርቦት ስምምነት መፈጸማቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ዘግበው ነበር፡፡ ነገር ግን ግበአቶቹን ለማቅረብ ተፈራርሟል የተባለው ተቋም የማይታወቅ እና በስራ ላይ የሌለ መሆኑንም አጋልጠዋል፡፡
የካራኮቭ ክልል ባለስልጣናት ብቻ 176.5 ሚሊዮን ዶላር መመዝበራቸውን የጸረ ሙስና ማህበረሰብ አንቂዎች መረጃዎችን ያወጡ ሲሆን በስም ከማይታወቅ ድርጅት፣በአንድ ሰው ባለቤትነት በተያዙ የተለያዩ ድርጅቶች እና በሌሎች የጨረታ ማጭበርበር ሂደቶች ገንዘቡ ተመዝብሯል ነው ያሉት፡፡
ሩሲያ በካራኮቭ ክልል ጠንከር ያለ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን ተከትሎ በስፍራው የሚገኙ የጦር መሪዎች ለሞስኮ ጦር መገስገስ የበላይ ሃላፊዎቻቸውን ተወቃሽ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም በውግያ ስፍራው ለመከላከያ ምሽጎች እና ለሌሎች ወታደራዊ ወጪዎች የተመደበው ገንዘብ እየደረሳቸው እንዳለሆነ ቅሬታቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
ተመዝብሯል የተባለውን ገንዘብ በተመለከተ ምርመራ እያከናወኑ የሚገኙት የሀገሪቱ ፓርላማ አጣሪ ኮሚቴ እና የህግ አስከባሪ አካላት ምርመራቸውን ቀጥለዋል፣ በቅርቡም ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የመንግስት እና ወታደራዊ ባለስልጣናትን ለፍትህ እናቀርባለን ብለዋል፡፡