ዛሬ ሁለት አመት በደፈነው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የተከሰቱ አበይት ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈትና ለጉዳት የዳረገው ጦርነት በአለማቀፍ ደረጃ የጎላ ተጽዕኖውን አሳርፏል
ጦርነቱ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዩክሬናውያንን ለስደት መዳረጉም ተገልጿል
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ዛሬ ሁለት አመቱን ደፍኗል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ማካሄድ መጀመራቸውን ያወጁት በፈረንጆቹ የካቲት 24 2022 ነበር።
ዘመቻው እንደተባለው በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ግን አልሆነም፤ በሁለቱም ወገን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈትና ለጉዳት ዳርጎ ሶስተኛ አመቱን አሃዱ ብሏል።
ጦርነቱ ከ10 ሺህ በላይ ንጹሃንን ህይወት ቀጥፏል፤ 20 ሺህ የሚጠጉትን ደግሞ አቁስሏል የሚለው የመንግስታቱ ድርጅት፥ የጦርነቱ ዳፋ “በቀጣዩ ትውልድ ጭምር የሚታይ” መሆኑን ገልጿል።
ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዩክሬናውያንን ከሀገራቸው አስወጥቶ ስደተኛ ያደረገው ጦርነት በአለም ምጣኔሃብት ላይ ያሳረፈው ተጽዕኖው በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
አለማቀፍ የማሸማገል ጥረቶች ቢደረጉም ከ18 በመቶ በላይ የዩክሬን ይዞታን በቁጥጥሯ ስር ያዋለችው ሞስኮ ከያዝኳቸው ስፍራዎች መልቀቅ አይደለም እስከ ኬቭ ድረስ ከመዝለቅ የሚያግደኝ የለም እያለች ነው።
የሃያላኑ መፋለሚያ ምድር የሆነችው ኬቭ ከምዕራባውያን የሚደረግላት ድጋፍ ለድል ሳያበቃት የጀመረችው መልሶ ማጥቃትም ስኬታማ አልሆነላትም።
ዛሬ ሁለተኛ አመቱን የያዘው ጦርነት እንዴት ተጀመረ? ምን ዋና ዋና ክስተቶች ነበሩ?
የካቲት 21 2022
- ሩሲያ ለዶኔስክ እና ሉሃንስ ግዛቶች ራስ ገዝነት እውቅና ሰጠች
የካቲት 24 2022
- ፕሬዝዳንት ፑቲን ሩሲያ በዩክሬን “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” መክፈቷን ተናገሩ
መጋቢት 4 2022
- ሩሲያ የዛፓሮዢያ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫን በቁጥጥር ስር አዋለች
ሚያዚያ 2 2022
- ዩክሬን የኬቭ ክልልን ሙሉ በሙሉ ከሩሲያ ማስለቀቋን ገለጸች
ሃምሌ 22 2022 - የጥቁር ባህል እህል ስምምነት
- በመንግስታቱ ድርጅት እና ቱርክ አደራዳሪነት በጥቁር ባህር የዩክሬን የእህል ምርትን ለማጓጓዝ ስምምነት ላይ ተደረሰ
መስከረም 21 2022
- ፑቲን 300 ሺህ ምልምል ወታደር እንዲመዘገብ አዘዙ (ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ግዙፍ)
መስከረም 30 2022 - የሩሲያ አራት ግዛት ጥቅለላ
- ሩስያ አራት የዩክሬን ክልሎችን(ዶኔስክ፣ ሉሃንስክ፣ ዛፓሮዢያ እና ኬርሰን) ወደ ግዛቷ ጠቅልላ ማስገባቷን አስታወቀች
ህዳር 9 2022
- ሩሲያ ጦሯ ከኬርሰን እንዲወጣ አዘዘች
ታህሳስ 21 2022 - የዜለንስኪ የአሜሪካ ጉዞ
- የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ሚስጢራዊ ጉዞ በማድረግ አሜሪካ ገቡ፤ የ1 ነጥብ 85 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ድጋፍም ቃል ተገባላቸው
ግንቦት 3 2023 - “ፑቲንን የመግደል ሙከራ”
- ሩሲያ በክሬምሊን አካባቢ ያንዣበቡ የዩክሬን ድሮኖችን መትቼ ጥያለሁ አለች፤ “የሽብር ጥቃት” ነው ያለችው ክስተት ፕሬዝዳንት ፑቲንን ለመግደል ያለመ እንደነበርም ገለጸች
ግንቦት 21 2023 - ባክሙት
- በዶኔስክ ግዛት የምትገኘው ባክሙት ከወራት ጦርነት በኋላ በሩሲያ በቁጥጥር ስር መዋሏ ተነገረ፤ ዜለንስኪ ለማመን ቢያመነቱም ከቀናት በኋላ ከኬቭ እጅ መውጣቷን አመኑ
ግንቦት 222 2023 - ቤልጎሮድ
- ዩክሬናውያን ታጣቂዎች ወደ ሩሲያዋ ቤልጎሮድ ክልል ዘልቀው ገቡ፤ የሩሲያን ድንበር ጥሰው መግባታቸውም ስጋት ፈጠረ
ግንቦት 25 2023 - ታክቲካል ኒዩክሌር
- ሩሲያ ታክቲካል ኒዩክሌር መሳሪያዎቿን በቤላሩስ ለማስፈር ስምምነት ተፈራረመች፤ “ለተስፋፊው ኔቶ” ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያግዛል ተባለ
ሰኔ 10 2023 - ተጠባቂው መልሶ ማጥቃት
- ዩክሬን በሩሲያ የተያዙባትን ይዞታዎች ለማስለቀቅ የመልሶ ማጥቃት መጀመሯን አወጀች (ይሁን እንጂ የረባ ውጤት ሳያሳይ ቀርቷል)
ሰኔ 24 2023 - የዋግነር አመጽ
- የሩሲያው ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ዋግነር ከዩክሬን ወደ ሩሲያዋ ሮስቶቭ ኦንዶን በመግባት ወደ ሞስኮ ግስጋሴ መጀመሩን ገለጸ፤ ከሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አመራሮች ጋር ጸብ አለኝ ያለው ቡድን ሞስኮ ለመድረስ 200 ኪሎሜትሮች ሲቀረውም በቤላሩስ ሸምጋይነት ወደኋላ አፈግፍጓል
ነሃሴ 2023 - የፕሪጎዥን ግድያ
- ዋግነር ባመጸ ልክ በሁለት ወሩ የቡድኑ መሪ ይቪግኒ ፕሪጎዥን የተሳፈረበት አውሮፕላን ተከስክሶ ህይወቱ አለፈ
ጥቅምት 7 2023 - የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት
- የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት መጀመር ዩክሬን ከምዕራባውያን የምታገኘውን የፋይናንስ እና ወታደራዊ ድጋፍ አቀዛቀዘ፤ መገናኛ ብዙሃኑም ትኩረቱን ወደ መካከለኛው ምስራቅ አደረገ
የካቲት 7 2024 - የተወዳጁ የጦር አዛዥ ስንብት
- ዜለንስኪ የዩክሬኑን የጦር አዛዥ ቫለሪ ዛሉዥኒ አባረሩ
የካቲት 17 2024 - ዳግማዊ ባክሙት አቪድቭካ
- የዩክሬን ጦር ከባድ ጉዳትን ለመቀነስ በሚል ከአቪድቭካ ከተማ ለቆ እንዲወጣ ታዘዘ፤ በማግስቱም ሩሲያ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሯን አስታወቀች