“ከህይወታችን 730 ቀናትን በጦርነት አሳልፈናል፤ በምርጧ ቀናችን እናሸንፋለን”- ፕሬዝዳት ዘለንስኪ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር የገጠመችውን ጦርነት 2ኛ ዓመት አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር “ዩክሬን ሩሲያን ታሸንፋለች” ብለዋል።
“ማናችንም ብንሆን ዩክሬን እንዲያበቃላት አንፈቅድም” ብለዋል ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ባደረጉት ንግግር።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት 2ኛ ዓመት እየታሰበ ያለው ዩክሬን ሩሲያን ከግዛቷ ለማስወጣት የምታደርገው ጥረት እንቅፋት እያጋጠመው ባለበት ሰዓት ነው።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ “ማንኛውም ሰው ጦርነቱ እንዲያበቃ ይፈልጋል፤ ጦርነቱ የሚቆመው ግን በዩክሬን አሸናፊነት እና የበላይነት ነው” ብለዋል።
“ከህይወታችን 730 ቀናትን በጦርነት አሳልፈናል፤ በህይወታቸችን ምርጧ ቀን እናሸንፋለን” ብለዋል ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በንግግራቸው።
ጦርነቱ 2ኛ ዓመቱን መድፈኑን ተከትሎ የጣሊያን፣ ቤልጂየም እና ካናዳ መሪዎች እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ዴር ሌይን አጋርነታቸውን ለመግለጽ ኪቭ ተገኝተዋል።
በጦርነቱ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተገኝተው የነበረ ሲሆን፤ ዘንድሮ በ2ኛ ዓመቱ ላይ አንድም የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን አለመገኘቱ ግርምትን ፈጥሯል።
ጣሊያን እና ካናዳ የጦርነቱን 2ኛ ዓመት አስመልክቶ ከዩክሬን ጋር አዲስ የደህንነት የጋራ መግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውም ነው የተገለጸው።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በትናንትናው እለት ሁለት,ተኛ ዓመቱን ደፍኗል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ማካሄድ መጀመራቸውን ያወጁት በፈረንጆቹ የካቲት 24 2022 ነበር።
ዘመቻው እንደተባለው በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ግን አልሆነም፤ በሁለቱም ወገን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈትና ለጉዳት ዳርጎ ሶስተኛ ዓመቱን አሃዱ ብሏል።
ጦርነቱ ከ10 ሺህ በላይ ንጹሃንን ህይወት ቀጥፏል፤ 20 ሺህ የሚጠጉትን ደግሞ አቁስሏል የሚለው የመንግስታቱ ድርጅት፥ የጦርነቱ ዳፋ “በቀጣዩ ትውልድ ጭምር የሚታይ” መሆኑን ገልጿል።
ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዩክሬናውያንን ከሀገራቸው አስወጥቶ ስደተኛ ያደረገው ጦርነት በአለም ምጣኔሃብት ላይ ያሳረፈው ተጽዕኖው በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
አለማቀፍ የማሸማገል ጥረቶች ቢደረጉም ከ18 በመቶ በላይ የዩክሬን ይዞታን በቁጥጥሯ ስር ያዋለችው ሞስኮ ከያዝኳቸው ስፍራዎች መልቀቅ አይደለም እስከ ኬቭ ድረስ ከመዝለቅ የሚያግደኝ የለም እያለች ነው።