ሩስያ ከኢትዮጵያ ጋር በዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መስራቷን እንምታጠናክር ላቭሮቭ ገለጹ
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከም/ጠ/ሚና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል
ሰርጌ ላቭሮቭ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ለጠ/ ሚኒስትር ዐቢይ የተላከ መልዕክት ለአቶ ደመቀ አቅርበዋል
የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኘት ትናንት ምሽት ጀምረወል።
በዛሬው እለትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ከውይይቱ በኋላ በሰጡት የጋራ መግለጫ ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን “በውይይታችን በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ያለንን ግንኙነት አጠናክረን ለመቀጠል ተስማምተናል” ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የሕዳሴውን ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር በተመለከተ አቶ ደመቀ፤ ኢትዮጵያ በመርህ ተመስርቶ ፍሬያማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያላትን አቋም ገልጸውላቸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስት፤ ሩ ሩስያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመርህን እና እውነትን በመከተል ለኢትዮጵያ ላሳየችው ድጋፍ አመስግነዋል።
የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከሩስያው ፕሬዚዳንት ክቡር ቭላድሚር ፑቲን ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተላከውን መልዕክት ለክቡር አቶ ደመቀ አቅርበዋል።
ሰርጌ ላቭሮቭ ኢትዮጵያ ከሩስያ ጋራ ባላት ውጤታማ ግንኙነት ደስተኞች ነን ብለዋል። የሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ እንዲካሄድ ሩስያ ፍላጎቷ እንደሆነም ገልጸዋል ።
ላቭሮቭ አክለውም፤ ሩስያ ከኢትዮጵያ ጋር በዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መስራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ማለታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በ4 የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝት እያደረጉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት በግብጽ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ እና ኡጋንዳ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በግብጽ በሰጡት መግለጫ፡ አሜሪካ በሩሲያ- አፍሪካ ግንኙነት ያለት ምክንያታዊ ያልሆነ ስጋት መተቸታቸው ይታወሳል።