“በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከሁለቱም ወገኖች 200 ሺህ ገደማ ወታሮች ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል”- የአሜሪካ ጀነራል
40 ሺህ ሲቪሎች በጦርነቱ መገደላቸውን የፕሬዚዳንት ባይደን የወታደራዊ ጉዳዬች አማካሪ ጀነራል ማርክ ሚሊ ገለጹ
አሃዙ ሞስኮም ሆነች ኬቭ ከሚጠቅሱት እንዲሁም ምዕራባውያን ከሚገምቱት እጅግ የተጋነነ ነው
ስምንት ወራት ያለፈው የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ከሁለቱም ወገኖች 200 ሺህ ወታደሮችን ሙትና ቁስለኛ መሆናቸው አልቀረም ሲሉ አንድ አሜሪካዊ ጀነራል ገምተዋል።
ጦርነቱ 40 ሺህ የሚጠጉ ንፁሃንን ህይወት ስለመቅጠፉም ነው የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቁልፍ የወታደራዊ ጉዳዬች አማካሪ ጀነራል ማርክ ሚሊ የገለፁት።
የጀነራል ሚሊ አሃዛዊ ግምት በሁለቱም ተፋላሚ ሀይሎችም ሆነ በምዕራባውያን ሲጠቀስ ከነበረው እጅግ የተጋነነ ነው።
ሞስኮ በመስከረም ወር 2022 ባወጣችው መረጃ 5 ሺ 937 ወታደሮቼ ተሰውተዋል ብላለች።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌ ሾጉ በምዕራባውያን የሚጠቀሰውን አሃዝም ከልክ በላይ ነው በሚል ውድቅ ሲያደርጉ ይደመጣል።
ሶቪየት ህብረት በፈረንጆቹ ከ1979 እስከ 1989 ከአፍጋኒስታን ጋር ባደረገችው ጦርነት የሞቱት ወታደሮች ቁጥር ከ15 ሺህ አይበልጥም መባሉም የጀነራል ሚሊ ግምት ጥያቄ ውስጥ ከሚከቱ ነጥቦች አንዱ ሆኖ ይቀርባል።
በጦርነቱ የሞቱ ወታደሮቿ ቁጥር ከመግለፅ የምትቆጠበው ዩክሬንም በነሃሴ ወር 9 ሺህ መድረሳቸውን ገልፃ እንደነበር ይታወሳል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ የጦርነቱ ተዋናዮች የሚያወጡት የጉዳት አሃዝ ተቀባይነት እንደሌለው በተደጋጋሚ ገልጿል።
ጀነራሉ በፈረንጆቹ የካቲት 24 2022 የተጀመረው ጦርነት ከ15 እስከ 30 ሚሊየን ሰዎችን ስደተኛ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ግን በጦርነቱ ምክንያት ወደ አውሮፓ ሀገራት የተሰደዱ ዩክሬናውያን ብዛት 7 ነጥብ 8 ሚሊየን እንደሚሆን ነው ያስታወቀው።
ጀነራል ማርክ ሚሊ አሃዙን ያጋነኑት ይምሰል እንጂ በጦርነቱ በሰውም ሆነ በንብረት ከፍተኛ ውድመት ደርሷል።
ድርድር
ሩስያ እና ዩክሬን ጦርነቱ እንደተጀመረ በሰላማዊ ንግግር ልዩነታቸውን ለመፍታት በቤላሩስ ያደረጓቸው ምክክሮች ውጤት አላመጡም።
የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቱርኳ አንታሊያ የነበራቸው ቆይታም የሰብአዊ እርዳታ ማስተላለፊያ መስመር እንዲከፈት ከማድረግ ውጭ ዘላቂ ተኩስ አቁምን አላመጣም።
የፈረንሳዩን ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጨምሮ የተለያዩ የሀገራት መሪዎች የአደራዳሪነት ሙከራም ሊሳካ አልቻለም።
ፑቲን ከስልጣን ካልተነሳ ድርድር የሚባል ነገር አይኖርም ሲሉ የሰነበቱት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዘለንስኪ፥ ከሰሞኑ ያሳዩት የአቋም መለሳለስ ግን የደበዘዘውን ተስፋ ብርሃን እየሰጠው ነው።
የኬቭ ወዳጅ አሜሪካም ጦርነቱ ያስከተለውን ውድመት በመጥቀስ ዩክሬን ወደ ድርድር እንድትመለስ እያግባባች ነው ተብሏል።