በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ፕሬዝዳንት ፑቲን ታመዋል ሞስኮም በአምሳያቸው እየተመራች ስለመሆኗ እየዘገቡ ይገኛሉ
ሩሲያ በፕሬዝዳንት ፑቲን አምሳያ እየተመራች ነው?
በዩክሬን በኩል ከምዕራባዊያን ጋር እየተዋጉ መሆናቸውን የሚናገሩት የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መታመማቸውን በርካታ ሚዲያዎች በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡
እነዚህ ሚዲያዎች አክለውም ፕሬዝዳንቱ በመታመማቸው ምክንያት ሩሲያ ፑቲንን መስለው በተሰሩ አምሳያ ሰዎች እየተመራች መሆኗንም አስነብበዋል፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሲሰጡ ስለ ፕሬዝዳንቱ መታመም ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ቃሎ አቀባዩ በምላሻቸው ፕሬዝዳንት ፑቲን በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸውን ገልጸው ስራ ከመብዛቱ ባለፈ የተለየ ነገር አልተፈጠረም ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን አምሳያ ሰው አላቸው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ፈጽሞ እንዲህ አይነት ነገር የለም ሲሉ በሳቅ ታጅበው ለጋዜጠኞች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከሶስት ዓመት በፊት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ላይ ጉዳዮ ተነስቶላቸው የነበረ ሲሆን በብዙዎች ዘንድ የሚነሳውን የአምሳይ ፑቲንን ጉዳይ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
የዋግነር አመራሮችን ይዞ ስለተከሰከሰው አውሮፕላን ፕሬዝዳንት ፑቲን ምን አሉ?
የ71 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ቤጂንግ አቅንተው ከቻይና አቻቸው ሺ ፒንግ ጋር መክረው ተመልሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከቻይና ጉብኝታቸው በኋላ የልብ ህመም አጋጠሟቸዋል በሚል የተሰራጨው ዘገባ ስህተት መሆኑን የክሪሚሊን ቤተ መንግስት ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡
የጅዶ ስፖርት አድናቂ እና ወዳጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፕሬዝዳንት ፑቲን ከ20 ቀናት በፊት 71ኛ ዓመት ልደታቸውን አክብረዋል፡፡
ላለፉት 20 ዓመታት ሩሲያን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ያሉት ቭላድሚር ፑቲን ወደ መሪነት ከመምጣታቸው በፊት የሩሲያ ደህንነት ባለሙያ ሆነው በተለያዩ ሀገራት አገልግለዋል፡፡