ፑቲን የሩሲያና ቻይና “ገደብ የለሽ” ትብብርን ለማጠናከር ቤጂንግ ገብተዋል
ፕሬዝዳንቱ በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዛዣ ከወጣባቸው በኋላ ሁለተኛውን የወጭ ሀገር ጉብኝታቸውን በቻይና እያደረጉ ነው
ሩሲያ በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት በምዕራባውያን ስትገለል ቤጂንግ ዋነኛ ወዳጇ ሆና ቀጥላለች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ጋር ለመምከር በዛሬው እለት ቤጂንግ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን እስከ ነገ በሚቀጥለው 3ኛው የአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ (ቤልት ኤንድ ሮድ) ፎረም ላይ ይሳተፋሉ።
የዩክሬኑ ጦርነት በቀጠለበት ወቅት ፑቲን ቤጂንግ መግባታቸው የቻይና እና ሩሲያን በመተማመን ላይ የተመሰረተና “ገደብ አልባ” ትብብር ያሳያል ተብሏል።
የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በመጋቢት ወት በፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ካወጣ በኋላ የዛሬው የቤጂንግ ጉዞ ሁለተኛው የውጭ ሀገር ጉብኝታቸው ነው።
ፑቲን በጥቅምት ወር መግቢያ በቀድሞዋ የሶቪየት ህብረት አካል ኪርጊስታን ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ቻይናም ሆነች ኪርጊስታን የአይሲሲ ፈራሚ አባል አለመሆናቸውን የሚጠቅሰው ሬውተርስ፥ ትልቅ ዜና የሚሆነው ፑቲን ወደ አይሲሲ አባል ሀገራት ጉብኝት ሲያመሩ ነው ይላል።
የእስር ማዘዣው በወጣ በቀናት ልዩነት ወደ ሞስኮ የዘለቁት ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ፑቲን ሀገራቸውን እንዲጎበኙ እና በ3ኛው የአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ ፎረም እንዲካፈሉ ያቀረቡላቸውን ጥሪ ተቀብለው ቤጂንግ ገብተዋል።
ፑቲን በነገው እለት በፎረሙ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉና ከፕሬዝዳንት ሺ ጋርም የሁለትዮሽ ምክክር እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ከተጀመረ ወዲህ ሞስኮ ከቤጂንግ ጋር ይበልጥ ግንኙነቷን አጠንክራለች።
ሩሲያ በየቀኑ ከ2 ሚሊየን በርሚል በላይ ነዳጅ ወደ ቻይና የምትልክ ሲሆን፥ ሁለተኛውን የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ መስመርም ለመገንባት አቅዳለች።
ቻይና የሩሲያን ነዳጅ በመግዛቷ 10 ቢሊየን ዶላር አተረፍኩ ማለቷም የሚታወስ ነው።
ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ወደ ቤጂንግ ያመሩት የሩሲያ ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያዎች ጋዝፕሮም እና ሮስኔፍት የስራ ሃላፊዎች ሁለተኛው የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ስለሚገነባበት ሁኔታ ይመክራሉ ነው የተባለው።