ዋግነር ግሩፕ ወደ ዩክሬን 50 ሺህ ወታደሮች ማዝመቱን አስታውቋል
የሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን በዩክሬን ምድር 10 ሺህ ወታደሮቹ እንደተገደሉበት ገለጸ።
ዋግነር የተሰኘው የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ቡድን ከሞስኮ ወታደሮች ጎን ሆኖ በዩክሬን እየተዋጋ ሲሆን በቅርቡ ባክሙት የተሰኘች ቁልፍ ከተማ ከዩክሬን ጦር ማስለቀቁ ይታወሳል።
የቡድኑ አዛዥ የቭግኔ ፕሪጎዚን በዩክሬን እያደረጉት ስላለው ውጊያ በተንቀሳቃሽ ምስል ባጋሩት ማብራሪያ እንዳሉት በዩክሬን ምድር ወታደሮቻቸው እንደሞቱባቸው ተናግረዋል።
ከሩሲያ የተለያዩ አካባቢዎች ባሉ እስር ቤቶች ባሰባሰቧቸው በጎ ፈቃደኛ ወታደሮችን ይዘው ወደ ዩክሬን መዝመታቸውንም ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ ወደ ዩክሬን 50 ሺህ ወዶ ዘማች ወታደሮችን እንዳዘመቱ የገለጹት አዛዡ እስካሁን 10 ሺህ ወታደሮች እንደተገደሉባቸው ተናግረዋል።
ይህም አሃዝ ሶቪየት ህብረት በአፍጋኒስታን ባደረገችው የ10 ዓመት ዘመቻ ወቅት ከተገደለባት 15 ሺህ ወታደሮች ጋር ሲነጻጸር በአጭር ጊዜ ብዙ ወታደሮችን ማጣቷ ተገልጿል።
ዋግነር በባክሙት ከዩክሬን ዘመናዊ ጦር ጋር ባደረጉት ውጊያ የሩሲያ ጦር እያገዛቸው እንዳልሆነ ሲተቹ መክረማቸው ይታወሳል።
በአፍሪካ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያሉት የዩክሬኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድሚትሪ ኩሌባ ሩሲያ በአፍሪካ ያላት ትልቁ ኢንቨስትመንት ቅጥረኛ ወታደሮችን ማሰማራቷ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የዋግነር ቅጥረኛ ወታደሮች ቡድን በሊቢያ፣ ማሊ እና ሱዳን መኖሩን ጠቅሰው አፍሪካ ከዩክሬን ጎን እንድትቆም ጠይቀዋል።