የኔቶ አባላት ሩሲያን ለማስፈራራት እየሞከሩ ነው- ፕሬዝዳንት ፑቲን
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከብሪታኒያው ጠ/ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጋር ተወያይተዋል
ምዕራባውያን በሩሲያ ጠል አመለካከት (ሩሶፎቢያ) መታወራቸውን ሞስኮው አስታውቃለች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) አባል ሀገራት በዩክሬን ውስጥ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ሩሲያን እያስፈራ ነው ሲሉ ለብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አሳወቁ።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በዩክሬን ጉዳይ ላይ በስልክ መወያየታቸውን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
በውይይታቸውም ፕሬዝዳንት ፑቲን አስተዳደራቸው በዩክሬን ዙሪያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው በዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በአሁን ላይ በዩክሬን ዙሪያ እየተፈጠሩ ያሉ ሁነቶች መነሻ የሩሲያን ደህንንት ስጋት ላይ በሚጥል መልኩ ኔቶ በዩክሬን ድንበር ውስጥ እያደረገ ያለው ወታደራዊ አቅም ማስፋፋት መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው ዩክሬንን አለመረጋጋት ውስጥ የሚያስገባ ማንኛውም እርምጃ ስትራቴጂካዊ ስህተት እና ያልተጠበቀ አደጋ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ እያደረገች ያለችው ወታደራዊ አቅምን የማጠናከር ተግባር ብሪታኒያን እንደሚያሳስባት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ያለውን ውጥረት ለመፍታት ዲፖሎማሲያው አማራጮችን ማየት ይገባልም ብለዋል።
የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት “ሩሲያ እስከ 175 ሺህ ወታደሮቿን በማሰማራት ጎረቤቷ የሆነችው ዩክሬንን በቀጣይ ዓመት መለውረር እየተዘጋጀች ነው” ሲሉ ይደመጣል።
ክሬምሊን በበኩሏ “ማንንም የመውረር እቅድ የለኝም” በማለት የአሜሪካን ውንጀላ ያጣጣለች ሲሆን፤ ምእራባዊያን በሩሲያ ጠል አመለካከት (ሩሶፎቢያ) ታውረዋል ብላለች።
ሞስኮ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) መስፋፋት ሩሲያን እንደሚያሰጋ የተገለፀች ሲሆን፤ በአውሮፓውያኑ በ1991 ለሩሲያ የተሰጡ ዋስትናዎችን የሚጥስ ነውም ብላለች።