“የዩክሬን ጦር ጦርነቱን ወደ ወራሪዋ ሩሲያ እየገፋው ነው” - ዘለንስኪ
ፕሬዝዳንቱ የሀገሪቱ ጦር ወደ ሩሲያ ግዛት በመዝለቅ ጥቃት በመፈጸም ላይ መሆኑን ተናግረዋል
በከርስክ ክልል እየተካሄደ የሚገኘውን ውጊያ ተከትሎ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የሀገራቸው ጦር ወደ ሩሲያዋ ከርስክ ክልል ዘልቆ በመግባት ጥቃት በመፈጸም ላይ መሆኑን አመኑ።
ፕሬዝዳንቱ በቴሌቪዥን በተላለፈ መልዕክታቸው የሀገሪቱ ጦር ጦርነቱን “ወደ ወራሪዋ (ሩሲያ) እየገፋው ነው” ብለዋል።
ዜለንስኪ ዩክሬን በከርስክ ክልል ከ1 ሺህ በላይ ወታደሮች፣ 11 ታንኮችና በርካታ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን በማስገባት ውጊያ ከጀመረ ከአምስት ቀናት በኋላ ነው ማረጋገጫውን የሰጡት።
በሩሲያ ግዛት ዘልቀው ጥቃት የፈጸሙትን ዩክሬናውያን “ጀግና ታጋዮች” በሚል ያወደሷቸው ዜለንስኪ፥ በሩሲያ ላይ ጫና የማሳደር ግብ ያለውን ዘመቻ በተመለከተ ከሀገራቸው ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ኦሌክሳንደር ሲርስኪ ጋር መምከራቸውን መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የሩሲያን ግዛት ከ10 ኪሎሜትር በላይ ጥሰው በመግባት ጥቃት ያደረሱትና ከሩሲያ ጦር እየተዋጉ የሚገኙት የዩክሬን ወታደሮች በርካታ መንደሮችን መቆጣጠራቸው ሲነገር ሰንብቷል።
ከትናንት በስቲያም ሱጃ የተባለችውን ከተማ መቆጣጠራቸውን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መልቀቃቸው የሚታወስ ነው።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ግን ከተማዋ አሁንም በሀገሪቱ ጦር ስር እንደምትገኝ በመግለጽ ድንበር ጥሶ የገባውን የዩክሬን ጦር በመደምሰስ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ሞስኮ “ወራሪ” ስትል የገለጸቻቸውን የዩክሬን ወታደሮች ከግዛቷ ሙሉ በሙሉ ለማስወጣት የሮኬት ማስወንጨፊያ እና ታንኮችን ጨምሮ በርካታ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ወደ ከርስክ ክልል ልካለች።
ከ76 ሺህ በላይ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ሩሲያውያንም በዩክሬን ጦር ድንገተኛ ጥቃት ሊደርስባቸው የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን ታስ የዜና ወኪል አስነብቧል።
በከርስክ፣ ቤልጎሮድ እና ባይራንስክ ክልሎች የሰዎችና ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የሚገድብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን፥ ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች የአየር ጥቃቷን በማጠናከር አጻፋዊ ምላሽ እየወሰደች ነው ተብሏል።
የዩክሬን ጦር ባለፈው ማክሰኞ ወደ ሩሲያ ዘልቆ መግባቱ “ከባድ ጸብ አጫሪ ድርጊት ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሞስኮ ስለምትወስደው የአጻፋ እርምጃ በይፋ አልተናገሩም።
ከኩርስክ ክልል ጋር 245 ኪሎሜትሮችን የምትጋራው ዩክሬን የሩሲያን ድንበር ጥሳ በመግባት ውጊያ መክፈቷ ለጊዜውም ቢሆን የጦርነቱን ሜዳና አቅጣጫ ለማስቀየር ቢያግዛትም የወታደሮቿን ቁጥር ግን ይበልጥ ሊያመናምንባት እንደሚችል ተገምቷል።