ዋግነር በደብዳቤው ቡድኑበምን ወንጀል እንደተከሰሰ የሚጠይቅ ነው።
የሩሲያው ዋግነር ቅትር ወታደራዊ ቡድን ለአሜሪካ ምላሽ ሰጠ።
የሩስያ የግል ወታደራዊ ቅጥረኛ ዋግነር ኃላፊ ለዋይት ሀውስ የፃፉት አጭር ደብዳቤ ዋሽንግተን በቡድኑ ላይ አዲስ ማዕቀብ ከጣለች በኋላ ኩባንያቸው በምን ወንጀል እንደተከሰሰ የሚጠይቅ ነው።
የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ከርቢ ዋግነር በዩክሬን ጦርነት የሩሲያ ጦርን ሲደግፍና ለጦር ሜዳ ድል ኃላፊነትን ሲወስድ የቆየ ትልቅ የወንጀለኞች ድርጅት ተብሎ ይሰየማል ብለዋል።
የዋግነር ቡድን መስራች የቨጀኒ ፕሪጎዚን በእንግሊዘኛ የጻፉት ደብዳቤ በቴሌግራም የትስስር ገጽ በኩል ለመገናኛ ብዙኸን የተላከ ሲሆን፤ ደብዳቤው በስም የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ከርቢን ጠርቷል።
"በዋግነር ቡድን ምን ወንጀል እንደተፈፀመ ግልጽ ማድረግ ይችላሉ?" ሲሉ ጠይቀዋል።
ቃል አቀባዩ ዋግነርን "ሰፊ ግፍ እና የሰብዓዊ መብት ረገጣ እየፈፀመ ያለ ወንጀለኛ ድርጅት" ብለውታል።
ባለፈው ወር ዋይት ሀውስ ዋግነር በዩክሬን የሚገኙ የሩስያ ጦር ኃይሎችን ለማጠናከር ከሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ ጭኖ እንደወሰደ ተናግሯል።
የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሪፖርቱን መሠረተ ቢስ ሲል ያጣጣለው ሲሆን፤ ፕሪጎዚን ሪፖርቱን “ወሬ እና መላምት” ሲሉ ገልጸዋል።
ዋሽንግተን በፈረንጆቹ 2017 እና ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ የጦር መሳሪያ መዳረሻን ለመገደብ ከዋግነር ጋር የሚደረገውን የንግድ ግንኙነት ገደብ አበጅታለች ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የአውሮፓ ህብረት በሶሪያ፣ ሊቢያ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሱዳን፣ ሞዛምቢክ እና ማሊ እንዲሁም በዩክሬን ሲንቀሳቀስ በነበረው ዋግነር ላይ እ.አ.አ በታህሳስ 2021 የራሱን ማዕቀብ ጥሏል።