የሩሲያ ጦር እና ዋግነር ፍጥጫ ወደለየለት ግጭት ያመራ ይሆን?
ተዋጊዎቹ በሩሲያ ጦር መገደላቸውን የገለጸው የዋግነር መሪው ይቪግኒ ፕሪጎዥን፥ በጦሩ አዛዦች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የአመጽ ጥሪ አስተላልፏል
ዋግነርን በወታደራዊ ተቋም ግልበጣ የከሰሰው የሩሲያ መንግስት በበኩሉ፥ በፕሪጎዥን ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል
በደቡባዊ ሩሲያ ውጥረት ነግሷል፤ የሩሲያው የቅጥረኛ ወታደር ቡድን ዋግነር ከዩክሬን ወደ ሩሲያ ገብቶ ሮስቶቭ የተሰኘችውን ከተማ አብዛኛው ክፍል መያዙን አስታውቋል።
በከተማዋ የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በታንክ የከበቡ ተዋጊዎቹን የሚያሳይ የቪዲዮ ምስልንም ለቋል።
ዋግነር በዩክሬን በሚገኙ ተዋጊዎቹ ላይ የሩሲያ ጦር የአየር ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ትናንት ምሽት በመሪው ይቪግኒ ፕሪጎዥን በኩል የአመጽ ጥሪ ማስተላለፉ ተነግሯል።
ፕሪጎዥን በድምጽ በተቀረጸ መልዕክቱ የሩሲያ ጦር መሪዎችን ለማስወገድ የትኛውንም እርምጃ እንወስዳለን ሲል መደመጡንም ሬውተርስ አስነብቧል።
ባክሙትን በማስለቀቁ ዘመቻ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉን እና ምክትላቸውን ተገቢውን ድጋፍ አልሰጡንም በሚል ሲወቅስ የነበረው ፕሪጎዥን ተገደሉ ስላላቸው ተዋጊዎቹ ቁጥርና ተያያዥ መረጃዎች በዝርዝር አልጠቀሰም።
በደቡባዊ ሩሲያ ሮስቶቭ የተጀመረው ከበባም እስከ ሞስኮ በመዝለቅ ወታደራዊ ተቋሙን እስከመቆጣጠር እንደሚደርስ ዝቷል።
የሩሲያ የፌደራል ደህንነት አገልግሎት የዋግነሩን መሪ እስከ 20 አመት ድረስ ለእስር በሚዳርግ የወታደራዊ ተቋም ግልበጣ ሙከራ ለመክሰስ ምርመራ ጀምሯል ተብሏል።
የዋግነር ድርጊትንም በዩክሬን እየተዋደቁ የሚገኙ የሩሲያ ወታደሮችን ከኋላ እንደመውጋትና የጠላት ተባባሪነት እንደሚቆጠር ነው የገለጸው።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴርም የፕሪጎዥን ውንጀላን “መሰረተ ቢስ እና ጸብ ጸጫሪ” ድርጊት ነው ብሎታል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭም ሁሉም የሩሲያ የደህንነት ተቋማት ከፕሪጎዥን ጋር የተገናኙ እያንዳንዱ እንቅስቃሴዎች ለፕሬዝዳንት ፑቲ ሪፖርት እያደረጉ መሆኑን መግለጻቸውን ታስ ዘግቧል።
ፕሪጎዥን ታድኖ እንዲያዝ መመሪያ መተላለፉንና ሞስኮን ከሮስቶቭ ዶን ከተማ የሚያገናኘው መስመርም በከፍተኛ ክትትል እንዲጠበቅ መታዘዙንም አብራርተዋል።
የሩሲያ ጦር አዛዦች የከፋ ችግር ከመፈጠሩ በፊት የዋግነር መሪው የአመጽ ጥሪውን እንዲያቆምና እጅ እንዲሰጥ እየጠየቁ ነው።
ፕሪጎዥን ግን የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሽዕጉ ጋር ፊት ለፊት እስካልተገናኘን ድረስ የሮስቶቭ ከተማን ዘግተን ወደ ሞስኮ መዝለቃችን አይቀርም የሚል የቪዲዮ መልዕክት ዛሬ ማለዳ መልቀቁ ተነግሯል።