በበዓሉ የሩሲያ ወታደራዊ አቅምን የሚያሳዩ ታንኮች፣ሮኬቶች እና አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ለእይታ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል
ሩሲያ በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመኑ ናዚ ላይ የተቀዳጀቸውን ድል የሚያስታውስ “የድል ቀን” በነገው እለት ግንቦት 1 ቀን 2014 ታከብራለች፡፡
የሩሲያ ባለስልጣናት ከዩክሬን ጋር እያካሄዱት ያለውን ጦርነት የዩክሬንን “ወታደራዊ አቅምን ለማዳከም” እና “የናዚ ስሜትን ለማጥፋት” የሚካሄድ “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ሲሉ እንደሚገልጹት የሚታወቅ ነው፡፡
በዚህም የክሬምሊን ሰዎች፤ ሞስኮ በዩክሬን ላይ እስካሁን የተቀዳጀቻቸውን ድሎች በክብር ለማሰብ ፤ በነገው እለት “የድል ቀን” ለማክበር የቤት ስራዎቻቸውን ለማከናወን ሽርጉድ ሲሉ ቆይተዋል፡፡
በዓሉ የሚከበረው በሞስኮ ብቻ ሳይሆን፤ሩሲያ ከከፍተኛ ውጊያ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በቁጥጥሯ ስር ባስገባቻቸው የዩክሬኗ ማሪዮፖል ከተማ ጭምር ነው ተብሏል፡፡
የዩክሬን ባለስልጣናት ለዚህ ስነ ስርዓት ሲባል የሩሲያ ወታደሮች የማሪዮፖል ዋና ጎዳናዎችን ሲያጸዱ መቆየታቸውንም ነው የተገለጸው፡
እንደ ባለስልጣናቱ ከሆነ መሃል ከተማ ከሚገኙ ጎዳናዎች ፍርስራሾች የማጽዳት ስራ ተካነውነዋል እንዲሁም ፤ አስሬኖች እና ያልፈነዱ ቦምቦች ተነስቷል፡፡
ዩክሬናዊቷ ፖለቲከኛ አልዮና ሸክሩም ሩሲያ የድል ቀኗን በምታከብርባቸው ቀናት ነገሮች የበለጠ ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ መናገራቸው የቻይናው የዜና ወኪል /ሺንዋ/ ዘግቧል።
"ለፑቲን እና መመስረት ለሚፈልጉት ግዛት ይህ ቀን ልዩ ትርጉም ይኖሯልም" ብሏል ፖለቲከኛዋ።
ፑቲን የድል በዓሉ በሚከበርበት ቀናት በኪቭ፣ ኦዴሳ እና ማሪዮፖል ከተሞች እና ዙሪያ ጠንካራ ውጊያ በመክፈት አስቸጋሪ የሚባሉ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ያላቸውን ስጋት አጋርቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ፤” ከሩሲያ ወረራ ጋር ክፋት ወደ ዩክሬን ምድር ተመልሷል ፤ ቢሆንም ግን ሀገሬ ታሸንፋለች” ሲሉ ተደምጧል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ሌሎች የጁ ሰባት(G7) መሪዎችም እንዲሁ ሰኞ በሩሲያ ውስጥ ከሚከበረው የድል ቀን በፊት አንድነትን ለማሳየት ከዘለንስኪ ጋር የቪዲዮ ንግግር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሩሲያ በነገው እለት የምታከብረው የድል ቀን ፤ በደማቅ ወታደራዊ ሰልፎች የታጀበ እንደሁም የሩሲያ ወታደራዊ አቅምን የሚያሳዩ ታንኮች ፣ሮኬቶች እና አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ለእይታ የሚቀርቡበት እንደሚሆን ተጠብቋል፡፡
በበዓሉ ፑቲን የሚያደርጉት ንግግር ስለ ጦርነቱ የወደፊት ሁኔታ ፍንጭ ሊሰጥ የሚችልም ሊሆን እንደሚችልም ከወዲሁ ተገምቷል፡፡