አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ምእራባውያን የፑቲንን በዓለ ሲመት ተቃውመዋል
ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያ ፕሬዝዳንት በመሆን በዛሬው እለት ለአምስተኛ የስልጣን ዘመን ቃለ መሃላ መፈጸማቸው ተነግሯል።
የፕሬዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዓለ ሲመት ዛሬ በክሬምሊን በተዘጋጀ ስነ ስርዓት የተካሄደ ሲሆን፤ ቭላድሚር ፑቲንም ለቀጣይ 6 ዓመታት ሩሲያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
በበዓለ ሲመት ላይ የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች፣ የሀገሪቱ ምክር ቤት አባላት፣ የሀገራት መሪዎች ተወካዮች፣ ዲፕሎማቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በበዓለ ሲመቱ ላይ ባደረጉት ንግግርም፤ “ሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እንደመሆኔ መጠን የዜጎችን መብቶች እና ነፃነቶች ለማክበርና ለመጠበቅ፤ የሩሲያ ፌዴሬሽን ሕገ-መንግስትን ለማክበር እና ለመጠበቅ እንዲሁም የሩሰያን የግዛት አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም በታማኝነት ለማገልገል ቃል እገባለሁ” ብለዋል።
“እኛ ሩሲያውያን ህብረት ያለን እና ታላቅ ህዝብ ነን” ያሉት የፕሬዝዳንት ፑቲን፤ “በአንድነት በመሆን ማንኛውንም መሰናክል እናልፋልን” ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን አከለውም መላው ሩሲያውያንን እንዲሁም ለዓባት ሀገራቸው በጦር ግንባር እየተዋደቁ ያሉ ሩሲያውያን ወታደሮችንም አመስግነዋ።
በዛሬው እለት በክሬምሊን የተካሄደውን የፕሬዝዳንት ፑቲን በዓለ ሲመትን አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ምእራባውያን ሀገራት ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ተቃውመውት ነበር።
ቭላድሚር ፑቲን እንደፈረንጆቹ ከ1999 ጀምሮ ላለፉት 25 ዓመታት ሀገሪቱን በፕሬዝዳንትነት እና በጠቅላይ ሚኒስትርነት መምራታቸው ይታወቃል።
የ71 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከወር በፊት በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ 88 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸው ይታወሳል።
በዚህም ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ ማለትም ለቀጣይ 6 ዓመታት በስልጣን ላይ የሚቆዩበት እድል በድጋሚ አግኝተዋል።