በጦርነቱ የተፈፀሙ ጥሰቶችን የሚያጣራው የተመድ ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ኢትዮጵያ መግባቱ ተገለጸ
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተሰተናገዱበት እንደሆነ የተመድ ሪፖርቶች ያመለክታሉ
መርማሪ ቡድኑ በሚቀጥሉት አምስት ቀናት በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ኢትዮጵያ መግባቱ ተገለጸ።
መርማሪ ቡድኑ በሚቀጥሉት አምስት ቀናት በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች ጉብኝት እንደሚያደረግም መቀመጫውን በጄኔቫ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትዊተር ገጹ ባጋረው ጽሁፍ አስታውቋል።
ሚሽኑ ከሳምንታት በፊት ባወጣው መግለጫ የመርማሪ ቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ መንግስት ባገኙት ፈቃድ መሰረት ሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ ወደ አዲስ አበባ የመሄድ እቅድ እንዳላቸው መግለጹ አይዘነጋም።
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ካሪ ቤሪሙሩንጊ “በአዲስ አበባ በሚኖረን ቆይታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወደ ተፈጸመባቸው አካባቢዎች መርማሪዎቻችን እንዲገቡ፣ ከጥቃት የተረፉትን እና የጥቃቱ ሰለባዎችን እንዲሁም ምስክሮችን እንዲያገኙ ፈቃድ ይሰጠናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለው እንደነበርም የሚታወስ ነው።
በዚህም መሰረት የመርማሪ ቡዱኑ አባላት ከአዲስ አበባ ውጭ ወደ ተላያዩ ሀገሪቱ ክፍሎች ጉዞ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ከህዳር 3 ቀን 2020 ጀመሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተፈጸሙ ወንጀሎችንና የመብት ጥሰቶችን ለማጣራት ስልጣን ያለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን ፤ እንደፈረንጆቹ ታህሳስ 17 ቀን 2021 ማቋቋሙ መሚታወስ ነው።
በተቋቋመው ዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶች መርማሪ ቡዱን ውስጥ የቀድሞ የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ ፋቱ ቤንሱዳ፣ ኬንያዊቷ ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ እና በሚቺጋን የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት አሜሪካዊ ስቲቨን ራትነር የኮሚሽኑ አባል ሆነው መሾማማቸውም ጭምር የሚታወቅ ነው።
ይሁን እንጅ ውስጥ የቀድሞ የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ ፋቱ ቤንሱዳ ባላፍነው ሰኔ 8 ቀን 2022 ከኮሚሽኑ ስለለቀቁ፤ ምክር ቤቱ ስሪላንካዊቷ ራዲካ ኩማራስዋሚን ማካተቱም ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች በተለያየ ደረጃ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግና የስደተኛ ህግ ጥሰቶችን መፈጸማቸውን የመብት ተቆርቋሪዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።