ድንበር ጥሰው የገቡ ከ209 በላይ የአልሸባብ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ
መንግስት የክልሉ ልዩ ሃይልና ፌደራል የጸጥታ ሃይሎች አልሸባብ ላይ የሚወስዱት እርምጃ ይቀጥላል ብሏል
አልሸባብ ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት “ከሸኔ” ጋር ለመገናኘት የነበረው እቅድ መክሸፉን መንግስት ገለጸ
ከቀናት በፊት "አቶ" በሚባለው ቦታ ወደ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን ገብቶ በነበረው የአሸባሪው አልሸባብ ታጣቂ ቡድን ላይ በተወሰደው እርምጃ አብዛኛው የቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውን መንግስት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ባወጣው መግለጫ፤ አልሸባብ በደረሰበት የተቀናጀ የማጥቃት እርምጃ የተበተነው ጥቂት ሃይልም የያዘውን ከባድ መሳሪያ መጨረሱንና ባገኘበት ቦታ ለመደበቅ እየሞከረ ይገኛል ብሏል።
እስካሁንም የሽብር ቡድኑ ይዞት ከመጣው 4 የረጅም ርቀት መገናኛ ሬዲዮ ውስጥ ሶስቱ መማረካቸውንም አስታውቋል።
ፌርፌር በተባለው አካባቢ በኩል ገብቶ ከነበረው የሽብር ቡድኑ ታጣቂ ውስጥም በ85ቱ ላይ እርምጃ ተወስዶ ሸሽተው ወደመጡበት ሲመለሱ በነበሩትም ላይ የጎረቤት ሃገር ሶማሊያ ፌደራል ሃይል የማያዳግም እርምጃ እንደወሰደባው በመግለጫው ተመላክቷ።
እስካሁንም ድንበር ጥሶ ከገባው ታጣቂ ሃይል ውስጥ ከ209 በላይ የሚሆኑት በክልሉና በፌደራል የጸጥታ ሃይሉ የተቀናጀ እርምጃ መደምሰሳቸውን መንግስት አስታውቋል።
በክልሉ ህዝብና ሚሊሻ እርምጃ የተወሰደበትና የተማረከውን የሽብር ቡድኑ አባላት ትክክለኛ ቁጥርም እየተጣራ መሆኑን መንግስት በመግለጫው አብራርቷል ።
የአልሸባብ የሽብር ቡድን በኤልከሬ ወረዳ አልፎ ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት ከሌላኛው የሽብር ቡድን ከሸኔ ጋር ለመገናኘት አልሞ የነበረ ቢሆንም ይህ እቅዱ ሙሉ በሙሉ መክሸፉ መንግስት በመግለጫው አረጋግጧል።
በተቀናጀው የመልሶ ማጥቃት የተበታተነውና ተቆርጦ የቀረውን የሽብር ቡድኑ ሃይል ላይ የሚወሰደው የማጽዳት ተልእኮ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
ባሳለፍነው ሳምንት "አቶ" በሚባል ቦታ ወደ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን የገባ የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን መደምሰሱን የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት ቅዳሜ እለት ማስታወቁ ይታወሳል።