የዩክሬንን ወታደሮች ከባክሙት ከተማ አያፈገፍጉም ሲሉ ዜለንስኪ ተናገሩ
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ከሲኤኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ባክሙትን መልቀቅ ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ያሉ ከተሞችን ለመያዝ መንገዱን ይጠርግላታል ብለዋል
አንዳንድ የዩክሬን የጦር አዛዦች ግን በባክሙት ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰ መሆኑና ተቆርጦ ሊቀር የሚችል ሃይል እንደሚኖር እያሳሰቡ ነው
የዩክሬን ወታደሮች በባክሙት ከተማ የሚያደርጉትን ትግል እንደሚቀጥሉ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከሲ ኤን ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ከበባ ውስጥ ያለችውን ከተማ መልቀቅ አደገኛ ነው ብለዋል
የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ባክሙትን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ካዋሉ ክራማቶርስክ እና ስሎቪያንስክ የተሰኙ ከተሞችን ለመያዝ መንገዱ ሁሉ ክፍት ይሆንላቸዋልም ነው ያሉት።
በባክሙት ለሳምንታት በዘለቀው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ከተማዋን ለቀው የወጡ ሲሆን፥ በከተማዋ መሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ውድመትም ቀላል አለመሆኑ ተገልጿል።
የከተማዋ በሩሲያ ወታደሮች መከበብም የዩክሬን ወታደሮችን ተቆርጠው እንዲቀሩ ሊያደርግ እንደሚችል አንዳንድ የሀገሪቱ የጦር አዛዦች እያሳሰቡ መሆኑን የሲ ኤን ኤን ዘገባ ያሳያል።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ግን ይህን አስተያየት አይቀበሉትም፤ “ከወታደራዊ መኮንኖች እየሰማውት ያለው መረጃ ይህን አይደለም፤ በቅድሚያ ማሰብ ያለብን ከበባ ውስጥ ስላለው ህዝባችን ነው” የሚል ምላሽም ሰጥተዋል።
በከተማዋ የትጥቅ አቅርቦቱን በማስፋት ዳግም መልሶ ማጥቃት ለመጀመርም እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል ዜለንስኪ።
ክራማቶርስክ እና ስሎቪያንስክ የተሰኙት ከተሞች በርካታ ነዋሪዎች ያሉባቸው የኢንዱስትሪ ከተሞች መሆናቸውም ከባክሙት አንጻር ስትራቴጂካዊ ፋይዳቸው ከፍ ያለ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች (ዋግነር) እና የዩክሬን ወታደሮች እየተፋለሙባት በምትገኘው ከተማ 4 ሺህ የሚጠጉ ንጹሃን አሁንም ድረስ መውጣት እንዳልቻሉ የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢርይና ቨርስቹክ ገልጸዋል።
ንጹሃኑ በምድር ቤት ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ በመሆኑም ከከተማዋ ማስወጣት ከባድ ሆኗል ብለዋል።
የባክሙት ከተማን ለሩሲያ ለቆ መውጣት ሌሎች የምስራቅ ዩክሬን ያዙልኝ እንደማለት ይቆጠራል ያሉት ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ፥ ንጹሃኑን የመጠበቅ ውጊያው እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።