በዩክሬን የሚገኙ የሩሲያ ታጣቂዎች ሁለት የሩሲያ መንደሮችን መቆጣጠራቸውን ገለጹ
"ኤፍአርኤል" እና "ሳይቤሪያን ባታሊዮን" የተሰኙት ቡድኖች ከሩሲያ ወታደሮች ጋር እየተፋለሙ መሆኑን የሚያሳዩ ምስሎችንም ለቀዋል
ክሬምሊን በበኩሉ የታጣቂ ቡድኖቹ ሙከራ መክሸፉን አስታውቋል
በዩክሬን የሚንቀሳቀሱ የሩሲያ ታጣቂ ቡድኖች ወደ ሩሲያ ዘልቀው በመግባት ውጊያ እያካሄዱ መሆኑን አስታወቁ።
በሩሲያ ቤልጎሮድ እና ኩርስክ ግዛት ሁለት መንደሮችንም መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል።
“ፍሪደም ኦፍ ሩሲያ ሌጊዮን” ወይም በምህጻሩ ኤፍአርኤል እና ሳይቤሪያን ባታሊዮን (ኤስቢ) ታጣቂዎቻቸው ከሩሲያ ወታደሮች ጋር ውጊያ እያካሄዱ መሆኑን ያሳያል ያሉትን ቪዲዮ ለቀዋል።
በቪዲዮው የኤፍኤርኤል ተዋጊ “ሌጊዮንን ከፑቲን አምባገነናዊ አገዛዝ ነጻ ማውጣት እንፈልጋለን፤ ምኞታችን እውን ለማድረግም የትኛውንም ጥረት እናደርጋለን፤ እያንዳንዱን ግዛታችን ሴንቲሜትር በሴንቲሜትር እናስመልሳለን” ሲል ይደመጣል።
“ኤስቢ”ም ከሩሲያ ወታደሮች ጋር በድንበር አካባቢ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ያሳያል ያለውን ቪዲዮ የለቀቀ ሲሆን፥ ከሶስት ቀናት በኋላ የሚካሄደውን የሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም ተቃውሟል።
ሌላኛው በዩክሬን የሚገኝ የሩሲያ ታጣቂ ቡድን “አርዲኬ” በበኩሉ ፥ “የክሬምሊን ወታደሮች ውጊያ ሳይጀምሩ ጭምር መሳሪያቸውን እያስቀመጡ ነው” ብሏል።
በዩክሬንና ሩሲያ ድንበር በኩርስክ ግዛት የምትገኘው ቴትኪኖ የተሰኘች ከተማ በዛሬው የታጣቂዎቹ ጥቃት ኢላማ ከሆኑትና ከተያዙት መካከል ትገኝበታለች።
በቤልጎሮድ ክልል የምትገኘው ሎዞቫያ የተሰኘች መንደርም በ”ነጻ አውጪዎች” በቁጥጥር ስር ሰለማዋሏ በዩክሬን የሚገኙት የሩሲያ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ኢልያ ፖኖማሬቭ ተናግረዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ራሳቸውን “ነጻ አውጪ” አድርገው የሚቆጥሩት ታጣቂዎች ያደረጉት ሙከራ መክሸፉን ገልጿል።
በቤልጎሮድ በሶስት አቅጣጫዎች የተደረገው የጥቃት ሙከራ በኬቭ የተቀነባበረና የተደገፈ ስለመሆኑም ነው ያስታወቀው።
የዩክሬን ጦር በበኩሉ ከዛሬው የታጣቂዎቹ ጥቃት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ይፋ ማድረጉን ቢቢሲ ዘግቧል።
በዩክሬን የሚገኙ የሩሲያ ታጣቂ ሃይሎች ሞስኮ በየካቲት ወር 2022 ጀምሮ ወደ ዩክሬን ዘልቃ ከገባች በኋላ ተደጋጋሚ ድንበር ዘለል የጥቃት ሙከራ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ባለፈው አመት ግንቦት ወር ላይም በቤልጎሮድ ክልል ተመሳሳይ የሰርጎ ገብ ጥቃት መፈጸማቸው አይዘነጋም።