ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬንን ጦርነት በአንድ ቀን ውስጥ ሊፈቱት እንደሚችሉ ተናገሩ
የዩክሬን ጦርነት ገንዘብ እና የጦር መሳሪያ በመላክ እንደማይፈታም ትራምፕ ገልጸዋል
ዶናልድ ትራምፕ ድርድር ጦርነቱን ማስቆሚያ ትክክለኛው መንገድ ነውም ብለዋል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬንን ጦርነት በአንድ ቀን ውስጥ እንደሚፈቱት ተናገሩ።
ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀረው የዩክሬን እና ሩሲያ አሁንም መቋጫ አላገኘም።
ምዕራባዊያን ሀገራት ዩክሬን የሩሲያን ጦር እንድትመክት በሚል የጦር መሳሪያ ልገሳቸው መቀጠሉን ተከትሎ ጦርነቱ እንደሚቀጥል የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።
ትራምፕ "ትሩዝ ሶሻል" በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንዳሉት "እኔ በፕሬዝዳንትነት ስልጣን ላይ ብኖር ኖሮ የዩክሬንን ጦርነት በ24 ሰዓት ልፈታው እችል ነበር" ብለዋል።
የዩክሬን ጦርነት ሚሊዮን ዶላሮችን እና የጦር መሳሪያቆችን በመላክ አይፈታም የሚሉት ትራምፕ "ድርድር ትክክለኛው መንገድ ነው" ሲሉም አክለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በነጩ ቤተ መንግሥት በነበራቸው የአስተዳድር ጊዜ ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንደነበራቸውም ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የዩክሬንን ጉዳይ የያዙበት መንገድ ትክክል አይደለም በሚል የሚተቹት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካዊያንን ገንዘብ ወደ ኬቭ መላክ የለበትም ሲሉ ጠቁመዋል።አሜሪካ ለዩክሬን ጦርነት እየሰጠችው ያለው ምላሽ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት እንዲነሳ የሚያደርግ ነውም ብለዋል።
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የፖለቲካ ጉዳዮች ሀላፊ ቪክቶሪያ ኑላንድ እንዳሉት ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ ከሆነች ዋሽንግተን በሞስኮ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች ለማንሳት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።