የሩሲያ ቢሊየነሮች ከ24 ባልበለጡ ሰዓታት ውስጥ 39 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማጣታቸው ተገለጸ
ጦርነቱ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ምድር ከፍተኛ የሆነ የገበያ ውድቀት እንዳያስከትል ተሰግቷል
ጄኔዲ ቲምቼንኮን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የሩሲያ ቢሊየነሮች ለተለያዩ የሃብት እገዳ እርምጃዎች ተዳርገዋል
የሩሲያ ቢሊየነሮች የዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ ከ24 ባልበለጡ ሰዓታት ውስጥ ከ39 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማጣታቸው ተገለጸ፡፡
ሩሲያውያኑ ቱጃሮች ከፍተኛ ኪሳራ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ቢጠበቅም በዚህ ደረጃ የከፋ ኪሳራ ያጋጥማቸዋል ተብሎ አልተገመተም ነበር፡፡
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሩሲያ በአክሲዮን ገበያ /MOEX/ የነበራት የግብይት ምጣኔ በ33 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ይህም በስቶክ ገበያ ታሪክ የከፉ ናቸው ከተባሉ ውድቀቶች 5ኛው ሆኖ ተመዝግቧል። ከፈረንጆቹ 1987 ወዲህ የታየ ከፍተኛ የገበያ ማሽቆልቆልም ነው የተባለው፡፡
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተጣሉና በመጣል ላይ ያሉ ማዕቀቦች በአውሮፓ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ምጣኔ ሃብታዊ ውድቀትን እንዳያስከትሉ ተሰግቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሃይል፣ በትራንስፖርት እና በመሠረተ ልማት ሀብት ላይ ኢንቨስትመንቶችን በማድረግ ላይ የተሰማራው ቮልጋ የተሰኘ የግል የኢንቨስትመንት ቡድን ባለቤት የሆኑት ሩሲያዊው ቢሊየነር ጄኔዲ ቲምቼንኮን ጨምሮ በሌሎች የሩሲያ ቱጃሮች ላይ ቀላል የማይባል የሃብት እገዳ ተጥሏል፡፡
ከግዙፉ የነዳጅ እና ጋዝ ቋሚ የተቀናጁ ኩባንያዎች አንዱ የሆኑነውን የLUKOIL ሊቀመንበር ቫጊት አሌኬሮቭ ሃብት በአንድ ቀን ውስጥ በአንድ ሶስተኛ ቀንሷልም ነው የተባለው፡፡
እንደ ብሉምበርግ ኢንዴክስ ከሆነ የቫጊት አሌኬሮቭ ሀብት በአንድ ቀን ውስጥ በ6.2 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በመቀነስ ወደ 13 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል፡፡
የሞስኮ የነዳጅ አምራችነት ድርሻ በትናትናው እለት ቀን በ33 በመቶ ገደማ ማሽቆልቆሉም ነው የተገለጸው፡፡
የብረታ ብረት አምራች የሆነውን ሴቨርስታል ሊቀመንበር የሆኑት አሌክሲ ሞርዳሾቭ 4.2 ቢሊዮን ዶላር ማጣታቸውን ተከለትሎ ሀብታቸው ወደ 23 ቢሊዮን ዶላር መውረዱም ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል ከ50 በላይ በሚሆኑ ሀገራት ውስጥ የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጥ ዓለም አቀፍ የኖሪልስክ ኒኬል (Norilsk Nickel) ኩባንያ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ ቁንጮ ሩሲያዊ ቱጃር ቭላድሚር ፖታኒን 3 ቢሊዮን ዶላር ማጣታቸውንም ዘገባዎች አመልክተዋል።